ቀጥታ፡

የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር ይገባል

ሚያዚያ 4/2014 (ኢዜአ) የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በሚጠበቅበት ልክ ውጤታማ እንዲሆን ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ ገለጹ።

የስራ እና  ክህሎት ሚኒስቴር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ዘርፉን ውጤታማ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል።

በመድረኩ የኃይሌ ሪዞርት፣ የኮሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ባለቤቶችን ጨምሮ በግል የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች ተገኝተዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ፤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በግል ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት እጥረት እንዳለ ይናገራሉ።

በዚህም የዘርፉ አንቀሳቃሾች የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ብቻ ሳይሆን ሰልጥነው ወደ ዘርፉ የሚገቡ ሙያተኞች ብቁ አለመሆናቸውን ቅሬታ እንደሚያቀርቡም አክለዋል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ምን አይነት ሙያተኛ እንደሚፈልግ ባላገናዘበ መልኩ ስልጠናዎች ስለሚሰጡ ነው ብለዋል።

የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ወደ ጎን ትቶ የሚሄድ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋም በዚህ መልኩ ከቀጠለ ያልተጣጣመ የሰው ኃይል አቅርቦት የሚያስከትል እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል።

ክፍተቶቹን ለመሙላት የማሰልጠኛ ተቋማትና በሆቴልና የቱሪዝም ዘርፉ የተሰማሩ አካላት በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በሀገሪቱ የሆቴልና ቱሪዝም ስልጠናዎች በስፋት የሚሰጡ ቢሆንም የስልጠና ስርዓቱ ውጤታማ ባለመሆኑ ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ ሊጫወት የሚገባውን ሚና እንዳልተወጣ ገልጸዋል።

ይህን ማካካስ የሚቻለውና በኢኮኖሚ ውስጥ የዘርፉን ሚና ማጎላት የሚቻለው ብቁ ባለሙያ ለኢንዱስትሪው ማቅረብ ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል።

በቀጣይ መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከሚሰሩ ባለሀብቶች ጋር በቅርበት እንደሚሰራም አንስተዋል።

የጀርመን መንግስት በቴክኒክና ሙያ ያላቸውን ልምድ፣ የምክር አገልግሎት፣ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅና የተለያዩ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ በትብብር እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ለዚህም የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም