ፋውንዴሽኑ የረመዳን ጾም ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 200 ችግረኞች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ፋውንዴሽኑ የረመዳን ጾም ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 200 ችግረኞች ድጋፍ አደረገ
ሚያዚያ 4/2014 (ኢዜአ) አል አማና የቲሞችና የችግረኞች መረዳጃ ፋውንዴሽን የረመዳን ጾም ምክንያት በማድረግ ከ1 ሺህ 200 ለሚበልጡ ችግረኞች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ፋውንዴሽኑ ከኢትዮጵያ ቅዱስ ቁርዓን ማህበር ጋር በመተባበር ነው ድጋፉን ያደረገው።
የፋውዴሽኑ መስራችና የኢትዮጵያ ቅዱስ ቁርዓን ማህበር ጸሀፊ አብዱልፈታህ ሙስጠፋ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ፋውንዴሽኑ ሶስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉም ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች በፋውንዴሽኑ አማካይነት የተሰባሰበ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ከማዕድ ማጋራቱ በተጨማሪ 15 ወጣቶችን በዘላቂነት ለማቋቋም መንጃ ፈቃድ እንዲማሩ የገንዘብ ድጋፍም አድርጓል፡፡
በማዕድ ማጋራት መርሃግብር ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ጸሃፊ ሼህ ሀሚድ ሙሳ በበኩላችን ይህን በጎ ተግባር ላከናወኑ ወገኖች ምስጋና አቅርበዋል።
ማህበረሰብ ሁሌም እርስ በርሱ ከተባበረ፣ ከተቻቻለና ከተረዳዳ ምንም ችግር ቢመጣ በቀላሉ መወጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
ይህን መሰል ስራዎች የሚሰሩ ማህበራትም ሆኑ ተቋማት ጋር ጽህፈት ቤቱ በጋራ እንደሚሰራና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚደርግ ጠቁመዋል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሽታዬ መሀመድ በበኩላቸው ይህን በጎ ተግባር ላከናወኑ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያውያንን ከምንም ጊዜ በላይ መረዳዳትና አብሮነት የሚጠይቅ ነውም ብለዋል ስራ አስፈጻሚዋ።