አጠቃላይ ሀገራዊ የጤና ወጪ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ደርሷል - ኢዜአ አማርኛ
አጠቃላይ ሀገራዊ የጤና ወጪ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ደርሷል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 4 /2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አጠቃላይ የጤና ወጪ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መድረሱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የክልል ጤና ቢሮ፣ የልማት አጋሮች፣ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮችና የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ስምንተኛ ዙር የኢትዮጵያ የጤና ወጪ ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል።
የጤና ወጪ ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና ለጤናው ዘርፍ የሚውለውን ኃብት ፍሰት ለመከታተል አገራት የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው።
በዚህም የወጣውን አጠቃላይ ሀብት ከመነሻው ጀምሮ ሀብቱ ለምን ጥቅም ላይ እንደዋለና በማን ጥቅም ላይ እንደዋለ በዝርዝር የሚያስረዳ ጥናት ነው።
በዚሁ መሰረት በ2009 ዓ.ም ይፋ የተደረገው ሰባተኛው ዙር የኢትዮጵያ የጤና ወጪ 72 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር እንደነበር ተገልጿል።
ይህም ባለፉት ዓመታት የ17 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት በማሳየት አጠቃላይ ሀገራዊ የጤና ወጪው ወደ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከፍ ማለቱ ተመላክቷል።
በስምንተኛው ዙር የጤና ወጪ ጥናት ውጤት መሠረትም የሀገሪቱ የጤና ወጪ በነፍስ ወከፍ ደረጃ ከነበረበት 33 ነጥብ 21 የአሜሪካ ዶላር ወደ 36 ነጥብ 3 የአሜሪካ ዶላር እድገት ማስመዝገቡ ተጠቅሷል።
የዓለም የጤና ድርጅት ካስቀመጠው የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ ጋር ሲነጻጸር ግን በጣም ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ካላቸው ሀገራት አንጻርም በ43 የአሜሪካን ዶላር ዝቅ እንደሚል ተነግሯል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አየለ ተሾመ፤ የጥናት ውጤቱ በተለያዩ የጤና ዘርፎች ላይ ወጪ የተደረገ ገንዘብ መጠን ለማወቅ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በቀጣይም መረጃው ሚኒስቴሩ በጤናው ዘርፍ ለሚቀርጻቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ጥቅም ላይ እንዲውል ይሰራል ብለዋል።
የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጡ አነስተኛ መስፈርቶችን በማሟላት የጤና ተደራሽነት ድርሻን ለማሳደግ ጥናቱ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ዘርፍ ቴክኒካል አማካሪው ኤርሚያስ ደሴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ 3 ነጥብ 63 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪ አድርጋለች ብለዋል።
የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ በሰባተኛ ዙር ከተካሄደው የ33 ነጥብ 21 የአሜሪካን ዶላር ወደ 36 የአሜሪካን ዶላር ማደጉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ሮዝ ማሬ ድላሚኒ፤ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል ዘላቂ የፋይናንስ ሥርዓትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች የምትገኘውን የጤና ማሻሻል ሥርዓት ለማረጋገጥ በቅንጅት መሥራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
በጤና ወጪ ጥናቱም የስነ-ተዋልዶ ጤና፣ የህፃናት ጤና፣ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ የቲቪ፣ የወባ እና ሌሎችም ተላላፊ ያልሆኑ የጤና አገልግሎቶች ወጪ መዳሰሳቸው ተነግሯል።