ቀጥታ፡

ኢትዮ-ቴሌኮም ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማዕከል ለአማራ ባንክ አከራየ

አዲስ  አበባ  ሚያዚያ 4 / 2014 (ኢዜአ) ኢትዮ-ቴሌኮም 'ሞጁላር የመረጃ ማዕከሉን የአማራ ባንክ በኪራይ መጠቀም እንዲችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።

የመረጃ ማዕከሉ የራሱ መጠባበቂያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያለውና በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚመራ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮ-ቴሌኮም የ80 ሚሊዮን ደንበኛን መረጃ መሸከም አቅም ያለውንና 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የፈጀበትን የዳታ ማዕከል አማራ ባንክ በኪራይ እንዲጠቀም ስምምነት ተፈራርሟል።

ይህም የባንኩን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት እጅግ ዘመናዊ እና ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችለዋል ተብሏል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የመረጃ ማዕከሉ በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚመራና ከፍተኛ አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ እንዳይስተጓጎል የሚያደርግ 99 በመቶ አስተማማኝ የኔትዎርክ አቅም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

የአማራ ባንክ ፕሬዝዳንት ሄኖክ ከበደ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ባንኩ ለሰነቀው ትልቅ ራዕይ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር የተደረገው ስምምነት ወደ ገበያ እየገባ ላለው አማራ ባንክ በቴክኖሎጂ የዘመነ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖረው ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከአማራ ባንክ በተጨማሪ በመረጃ ማዕከሉ አገልግሎት እያገኙ ያሉ 84 ድርጅቶች እንዳሉ ተጠቅሷል።

ኢትዮ-ቴሌኮም አሁን ካሉት ሁለት የሞጁላር የመረጃ ማዕከላት በተጨማሪ ሦስት ማዕከላት በግንባታ ላይ እንዳሉ ኩባንያው አስታውቋል።

አማራ ባንክ 188 ሺህ ባለአክስዮኖች ያሉት ሲሆን 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል እና ቃል የተገባ 7ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ መጠን አለው ተብሏል።

ባንኩ አሁን ያለው ካፒታል በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ የሚባል ሲሆን በሀገሪቱ ከሚገኙ የግል ባንኮች ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ ያስችለዋል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም