ቀጥታ፡

በወረዳው በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች መጠለያ ቦታ የማዘጋጀትና ሰብአዊ ድጋፍ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው

ሠመራ፤ ሚያዚያ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ሃሪ-ረሱ ዞን ሰሙሮቢ-ገለአሎ ወረዳ ኩማሜ ከተማ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች መጠለያ ቦታ የማዘጋጀትና ሰብአዊ ድጋፍ የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ወረዳው አስታወቀ።

በከተማው የእሳት ቃጠሎው የተከሰተው ትናንት ከቀኑ 11 ሰዓት አካበቢ ከአንድ መኖሪያ ቤት መሆኑ ታውቋል።

በአደጋውም 80 ሱቆችን ጨምሮ 175 ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ሲያወድም በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን የወረዳው ፖሊስ ወንጀል መርማሪ ሳጂን አደም ገባጌዴ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በከተማው የእሳት አደጋ መከላከያ ባለመኖሩ እንዲሁም በአካባቢው ከነበረው ከፍተኛ ንፋስ ጋር ተዳምሮ የእሳት ቃጠሎውን ለመቆጣጠር አስቻጋሪ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት ማደረሱን አስረድተዋል።

አደጋው በተከሰተበት አካባቢ የነበሩ የቤንዚንና ሌላም ነዳጅ መሸጫ ቤቶች መኖራቸው ለቃጠሎው መባባስ ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የእሳት ቃጠሎ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ በአካባቢው ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት ትብብር መቆጣጠር መቻሉን ገልጸው፤ የቃጠሎ መንስኤ ከኤሌክሪክ ጋር በተያያዘ እንዲሆነ ቢገመትም ለማጣራት ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአደጋው ምክንያት ንብረታቸው የወደመባቹው ወገኖች መጠለያ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀሰን ሀንዴ ገልጸዋል።

ይህም ሆኖ አልባሳት፣ ምግብ ነክና መጠጥ ውሃ በአፋጣኝ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመው፤ ተጉጂዎችን ለመደገፍ በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ህብረተሰብ በመደገፍ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም