የጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል
ሚያዝያ 04/ 2014 (ኢዜአ) የጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ተናገሩ።
የጃፓን መንግሥት ለሰላም ሕጻናት መንደር የጨርቃ ጨርቅ ማሰልጠኛ ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ የሚውል 49 ሺህ ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
ጎን ለጎንም 10 የስፌት ማሽንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለማሰልጠኛ ተቋሙ ድጋፍ ማድረጉን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ የጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብታዊ እድገትና የሰው ኃብት ልማት መሻሻል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ጃፓን መንግሥት ከ400 በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በመሥራት ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።
በተለይም ደግሞ የጃፓን ልማት የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የበኩሉን እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል በጥራትና በብዛት ለማፍራት እየሰራ መሆኑን የማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጫሊ ተናግረዋል።
የጃፓን መንግሥት ያደረገው ድጋፍ ተቋሙ በርካታ ሰው ተቀብሎ ለማሰልጠን ያስችለዋል ብለዋል።
የተጠናቀቀው ይኸው የማስፋፊያ ግንባታ በዓመት 200 ተማሪዎችን በተጨማሪ ለማሰልጠን ዕድል እንደሚፈጥርለት ጠቁመዋል።
በዚህም ለአገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕከሉ ሠልጣኞች በበኩላቸው ሥልጠናው ክህሎታቸውን እያጎለበተላቸው መሆኑን ጠቁመው ያገኙትን የሙያ ሥልጠና ሥራቸውን ለማጠናከር እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል።