ኢትዮጵያ -ፈተናዎቿና ተስፋዎቿ

ከብርሃኑ ተሰማ(ኢዜአ) የዘመኑ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሚያደርሱን መረጃዎች አንዳንዶቹ በአነጋጋሪነታቸው፣ በአስቂነታቸውና በአስገራሚነታቸው ያስደምሙናል። እያጠናቀቅን ባለው ዓመት አጋማሽ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፤ታክሲ ተሳፋሪው የአገሩ ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳስበው ዜጋ ነበርና በጉዞው ላይ ሳለ “ይህቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?’’ በማለት በውስጡ የነበረውን እምቅ ስሜት ሳይታወቀው ይተነፍሳል፤ አንዳንዴ እንደሚያጋጥመን ሁሉ። ይህንኑ የሰማው የታክሲ ረዳቱ ተሳፋሪው አቅጣጫው የጠፋበት መስሎት “የት ብለህ ነው የተሳፈርከው?” ብሎት አረፈው። በተሳሳተ የታክሲ መሥመር የገባ መንገደኛ መስሎት። የጽሁፌ መንደርደሪያ የሆነውን ቀልድ መሰል እውነታ ያገኘሁት ከአንዱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ወዳጄ ነው፡፡ አዎን አገራችን ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይም እስከ 2010 አጋማሽ የነበረችበት ሁኔታና ያሳለፈቻቸው ችግሮች ተሳፋሪውን እንዳስጨነቀው “ወዴት እየሄድን ነው?’’ ብሎ ቢያስጨንቀው ሳይታሰብም ቢያናግረው አይገርምም፤ አይደንቅምም። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ወዳጆቻችንን ያስጨነቀ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷልና። አገሪቱ በነዚህ ዓመታት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ገንፍለው የወጡባት ሁኔታ አጋጥሟታል። ውስጣችንን ሲበሉ የነበሩ ችግሮች ወጥተዋል። ችግሮቹ እንደ አገርና እንደ ሕዝብ አብረን ለመኖርና ህልውናችንን ለማስቀጠል ስጋታችንም ነበሩ። ኢትዮጵያውያን የቀድሞ ማንነታችንንና የሥልጣኔ ቁንጮነታችንን በመዘንጋት፣ አንዳችን በሌላችን ላይ ባደረስናቸው በደሎችና ችግሮች አብረን ያልኖርንና የማንተዋወቅ የሚያስመስሉ ተደርገንም ተፈርጀናል።ይህም እኛን አይገልጸንም ብለናል። መልካም ነገሮቻችን ሳይቀር ጥላሸት እየተቀቡ ልዩነቶቻችንን ለማስፋትና ለመነጣጠል ጫፍ የደረስን እስከሚመስለን ድረስ ተሞክሯል። ሕዝቡ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ነበሩበት። ፍትህ ማጣትና ሙስናም ሲያማርሩት ቆይቷል። በምሬቶቹ ወደ አመጽ በሚገባበት ደረጃ ላይ ደርሶ ሕይወቱን ለመስጠትም የተገደደበት ሁኔታም ታይቷል። በዚያ በተጨናነቀ ሁኔታ የአገሩ ጉዳይ ያሳሰበው ወንድማችን የውስጥ ስሜቱ ገንፍሎበት “ወዴት እየሄድን ነው?’’ ቢል ምን ይደንቃል?! መሪውን ፍለጋና ውጤቱ ወቅቱ ኢትዮጵያውያን ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በውስጥ ችግሮቻችን መነሻነት እየተከሰቱ ባሉት ሁኔታዎች ጥሩ ዜና የሚሰማበት አልነበረም። “የዚህች አገር ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?’’ ብሎ መጨነቅና መጠበብ የዜጎች የዕለት ከዕለት ሥራ ሆኖም ነበር። በዚሁ ሁሉ መሃል ግን ተስፋ ይታያል። አገሪቱን ወደ አንድነቷ የሚመልስ መሪ ማግኘት። የአስቴር ዐወቀ ’’አንድ አድርገን’’ የሚለው ዜማ በያለበት ይሰማል። ታሪከኛው 2010 ዓመት በትርምስና በችግሮች፣ በጭንቀትና ባለመረጋጋት ሲናጥ አገሪቱን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ለችግሮቹ መፍትሄ ለማፈላለግ ሲመክርም ቆይቷል።የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሥልጣን መውረድ ጥያቄን ተከትሎ የተሰበሰበው የኢህአዴግ ምክር ቤት የሊቀመንበርነት ምርጫ ውጤት ደግሞ ከወትሮው በተለየ በጉጉት የሚጠበቅ ሆነ። “የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን የሚረከበው ሰው የሕዝቡን ጥያቄዎች የሚመልስና የአገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቅ ይሆን ወይ?’’ የሚለው ዋነኛው ጉዳይ ነበር። ምክር ቤቱ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታና የሕዝቡን ፍላጎት ባስከበረ መልኩ የመረጠው መሪም የአገሪቱን አንድነት የሚያጠናክር፣ ገናናነቷን ለመመለስ የሚሰራ፣ በፓርቲውና በመንግሥት ለተፈጸሙ ጥፋቶች ይቅርታ የሚጠይቅና የመጪውን ጊዜ ተስፋ የሚያመላክት ሆኖ ተገኘ። መሪው ከአምስት ወራት በፊት በፓርላማ ቀርበው ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ወቅት ባሰሙት ንግግራቸው “ኢትዮጵያ’’ የሚለውን የአገራችን መጠሪያ ደጋግመው ሲጠሩ ሕዝብ ልብ ውስጥ ገቡ። የአንድነት መሪነታቸውን ባሳዩበት መድረክም ችግሮቻችን ሊፈቱ እንደሚችሉም ሲገልጹ፤ ተስፋውን አለመለሙት። ሕዝቡም አነሰም አደገም ላሉበት ችግሮች መፍትሄ የሚያፈላልግ መሪ ብቅ በማለቱ እፎይ ማለት ጀመረ። አዲሱ መሪ ሥልጣን በተረከቡ የመጀመሪያው ሳምንት አንድ ፀሐፊ በፎርቹን ጋዜጣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድን ከዓለማችን ታላላቅ መሪዎች ጋር በማወዳደር እንዲህ ብለው ጽፈዋል። “ዕድሜያቸውና አመለካከታቸው ከኢማኑኤል ማክሮን ጋር ይመሳሰላል። ተስፋ አድራጊነታቸውና የግንኙነት ጥበባቸው የኦባማን ውጤት ያስገኝላቸዋል። በውትድርናና በደህንነት መስኮች መሥራታቸው የፑቲን ዓይነት ልምድ ይሰጣቸዋል። ብዝኃነትን ለማስተናገድና ለእርቅ ያላቸው ትኩረት የኔልሰን ማንዴላን ዓይነት ውጤት እንደሚያመጣላቸው አልጠራጠርም።አዳዲስ ነገሮችን ለመቀበል ያላቸው ፍላጎት ከአንጌላ መርክል ይመሳሰላል። መንግሥታቸው ጥፋት ሰርቶ ቢገኝ፤ እንደ ሺንዞ አቤ ይቅርታ መጠየቅ አይገዳቸውም። አስተዳደራቸውን ሕዝብ የማይቀበልበት ደረጃ ቢደርስ እንኳን፤ እንደ ዴቪድ ካሜሩን ሥልጣናቸውን አስረክበው ከመውረድ ወደኋላ የሚሉ አይመስለኝም’’ ብለዋል። መሪው በተከታታይ በክልሎች እየተዘዋወሩ ከተለያዩ ብሄረሰቦች ከተውጣጡ አገር ሽማግሌዎችና ሕዝብ ተወካዮች ጋር ባደረጓቸው ስብሰባዎች “ሁሉም ለኢትዮጵያ” ዋልታና ማገር መሆናቸውን በክልሎቹ የሥራ ቋንቋዎች ጭምር በመናገር እያሳዩ፣ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የፌደራል መንግሥት ድጋፍ እንደማይለያቸው እያረጋግጡ ገቡ። ኢትዮጵያዊነት እንደሚለመልም እንጂ፤ ሞቶ እንደማይቀበር ምልክትም ሆኑ። ንግግራቸው የሚናፈቅ፣ አስተሳሰባቸው ምጡቅ፣ የአብሮነት ዓርማ በመሆናቸውም በዓለም ዙሪያ ያሉት ዜጎች ሳይቀሩ የአዲሱን መሪ ውሎ መከታተል የዕለት ሥራቸው ሆነ። ብሎም ተከታያቸው መሆንም ያዙ። በመላው አገሪቱና በውጭ የተካሄዱት የድጋፍ ሰልፎች ለዚህ ሁነኛ ምስክሮች ናቸው። ከጎረቤት አገሮች ጋር የነበረው ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ሆኖ እንዲቀጥልም ጉብኝቶች አደረጉ። በተለይ ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት በአዲስ መልክ መቀጠሉ ሰላምን የወለደና ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን፤ ለኢኮኖሚውም፣ ለፖለቲካውም፣ ለማህበራዊና ለሕዝብ ሕዝብ ግንኙነቶች ተጠርቅሞ የነበረውን በር ከፈተው።ተነጣጥለው የነበሩ ቤተሰቦች የተቀላቀሉበት የሚመስል መፈላለግና መዋደድ እንዳላቸው በሁለቱም አገሮች ዜጎች ላይ ታይቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ለገላጋይ አስቸግሮ የቆየው የሁለቱ አገሮች ግጭት በመሪዎች ጥረት በመፈታቱ የአጎራባች ክልሎችን የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመመለስ አስችሏል። የሶማሊያና የደቡብ ሱዳን መሪዎች ኤርትራን ለመጎብኘትና የጋራ ስምምነቶች ለመፈራረም አብቅቷቸዋል። በቀጣይ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንደሚፈጥርም ይጠበቃል።ዘመኑ የሚጠይቀውን በሰላም አብሮ የመኖርና ተባብሮ የማደግ ፍላጎታቸውን ላሳዩት መሪዎች ምስጋናና አድናቆቴ ይድረስልኝ። በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችና ሳዑዲ ዓረቢያ ያደረጓቸው ጉብኝቶችም በተለመደው መልኩ የተከናወኑ አልነበሩም። የአገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም የሚያጎለብት ድጋፍ የተገኘባቸውና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር መሠረት ያስቀመጡ ነበሩ። በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መቼም ግብጻውያንን እንደማይጎዳ ያረጋገጠቡት ነበር። በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚገነባው ግድብ ዋነኛ ዓላማ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንጂ፤ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ውሃ ለማሳጣት ታስቦ እንዳልተጀመረ በአዲሱ መሪያችን ዳግም ተገልጾላቸዋል። ኢትዮጵያ የዓባይ ልጆች ትብብር በሁለንተናዊ መልኩ እንዲያድግ የአገራቸው ፍላጎቷ መሆኑንም አመልክተዋል። መሪያችን በአሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት አገራቸውንና ወገናቸውን የናፈቁትን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያገናኘ፣ ዛሬም የሚኮሩባት አገር እንዳለቻቸው ያመለከተ፣ ለልማቷና ለዕድገቷ መቆማቸውን ያረጋገጡበት ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አፍላቂነት የተቋቋመው የ“ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ’’ን በቀን በአንድ ዶላር ሳይሆን፤ ወደ 10 ዶላር እንደሚያድግም በአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ መገለጹ ይታወሳል። በዓረብ አገሮች ያሉት ዜጎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ወገንን ለመደገፍ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉት ዜጎችም የአገራቸውን ዕድገት ለማፋጠን እገዛ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል። አገራቸውን ባላቸው የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያና በሌሎችም ምክንያቶች ለማየት ሳይችሉ አስርታትን ያስቆጠሩት ዜጎችም ‘’ማን እንደ እናት ፤ማን አንደ አገር’’ ብለው መጉረፍ ጀምረዋል።በተለይ አዲሱን ዓመት በአገራቸው ለመቀበል የሚመጡትን ማየቱ በቂ ነው። ፈተናው:- ለውጥ እንደ ስሙ የመለወጥ ጉዳይ በመሆኑ ለውጡ ያልተመቸው፣ ቶሎም ለመቀበል የሚቸገር አካል ይኖራል። ለውጡን እንደተቃወመ የሚኖር ወገን ይኖራል። ለውጥ መቼም ለመልካምና ለብዙኃን ጥቅም ከሆነ፤ መቀበልና ማስቀጠል እንጂ፤ ለማደናቀፍ መንቀሳቀስ ተገቢ አይሆንም። ከሦስት ዓመታት በላይ የቆዩትን የአገራችንን ችግሮች ለመፍታት የተያዘው መንገድ ያጋጠመው ፈተናም በለውጡ የመነካትና ተጠቃሚነትን በማጣት መነሻነት ግጭቶችን በተለያዩ አካባቢዎች መፍጠር ሥራቸው ያደረጉት ይመስላል። አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ስትገባ ያልተመቻቸው ወገኖች ከዚህም ከዚያም ብቅ በማለት “ተነካህ’’ የሚሉትን ብሄር/ብሄረሰብ ከዚያም ወርዶ ጎሳ ይዘው ለመንቀሳቀስ ጥረዋል። ሃይማኖትን ለዚህ እኩይ ዓላማ ለማዋልም ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፤ ይስተዋላልም። ማንነትን መሠረት ባደረገው የኢፌዴሪ መንግሥት የተዋቀሩት ክልሎች በአንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ የጋራ አገር ለመገንባት እንጂ፤ አንዳንዶች አሁን እያመጡት እንዳለው አስተሳሰብ አንዱን ከሌላው ለይተው ለማኖር የተፈጠሩ አለመሆናቸው በተግባር መረጋገጥ አለበት። ክልልን በአንድ እንደ መከለል አድርገው ማሰብና ጠባብነትን የሚያስተናግድ አስተሳሰብም እየተስተዋለ ነው። “በክልሌ ሌሎች ሊኖሩ አይገባም’’ የሚል አጉል አስተሳሰብ መወገድ አለበት።ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት።ዜጎቿም በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው የመኖርና የመሥራት ህገመንግስታዊ መብት እንዳላቸው ማስተማር ያስፈልጋል። የፌደራል መንግሥት የሕግ የበላይነትን ባለማስከበርና አጥፊዎችን ለፍርድ በማቅረብ ቸልታ ይታይበታል ተብሎም ይወቀሳል። የይቅርታና የምህረት ወቅት ነው ተብሎ ብዙ ታልፏል። የፍቅርና የመደመር ዘመን ነው ተብሎ የታለፉ እንዳሉም ይታመናል። ለሁሉም ልክ አለውና የዜጎችን ህልውናና ንብረት ለመጠበቅ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂዎችን በሕግ መዳኘት ያስፈልጋል። በአገሪቱ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማረጋገጥ ተብሎ የተወሰዱት እርምጃዎችን ባለመረዳትና በቆየ አስተሳሰብ በመመራት የትጥቅ ትግላቸውን አቁመው ወደ አገር ውስጥ ለመግባት ከመንግሥት ጋር ስምምነት የደረሱትን የፖለቲካ ድርጅቶች አቋም ባለማወቅም ይሁን ሆን ተብሎ በአፍራሽ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ወገኖችም በአንዳንድ ክልሎች አጋጥመዋል። ነፃነትና ሥርዓት አልበኝነትን እያደባለቁ ባሉት ዜጎችም ሕይወት ያለአግባብ አልፏል። ሀብትና ንብረት ወድሟል። ድርጊቱ በአገሪቱ ሕዝቦች ባህልና እምነት ውስጥ የማይታወቅና ተቀባይነት ስለሌለውም መግታት ያስፈልጋል።አንዱን ብሄር/ብሄረሰብ ከሌላው በመለየት ለማጥቃት የሚሞክሩና በዘረኝነት በሽታ የተለከፉ ወገኖችም ከድርጊታቸው እንዲገቱ ማድረግ ተገቢ ይሆናል። በአገሪቱ ከዝርያ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሥራዎች ካሉ በእህል፣በጥራጥሬ፣በአትክልትና ፍራፍሬና በእንስሳት ዝርያዎች ላይ በአብዛኛው ምርታማነት የሚያድግባቸው ሙከራዎች ናቸው። ዓለም አንድ እየሆነችበት ባለችበት ዘመን ሕዝብ የሚተባበረው ለጋራ ጥቅም ለሚበጁ፣ ለብልጽግና ሕይወቱን ለመቀየር መሆን ሲገባው፤ በጥፋት ስምሪት ላይ መሆኑ ያለአዋቂነትንና የዚህን ኩሩ ሕዝብ ማንነት ያለመረዳት ነው። እንደ ኢትዮጵያ በኅብረ ብሔራዊነት በተሳሰረ አገር ሕዝቦችን ለማለያየት ታስቦ የሚሰራ ከሆነ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዳለው ማወቅ ይጠቅማል።በሕግም ያስጠይቃል። ከምንምና ከማንም በላይ ደግሞ ማንንም አይጠቅምም። ተስፋውና ዕድሎቹ:- ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮና የሰው ሀብት ለዜጎቿ የምትበቃ አገር ናት። አልፋ ተርፋም ለጎረቤቶቿ ልማትና ዕድገት ብሎም ሰላማቸው እንዲረጋገጥ የምትጥር መሆኗን ከመሪዎቹና ከሕዝቦቹ አንደበት መስማት የተለመደ ነው። ለኢንቨስትመንት ባላት ምቹነትም ዜጎቿና የውጭ ባለሀብቶች ሰርተው ራሳቸውንና አገሪቱን ለመለወጥ እንደሚችሉ ይታወቃል። ሕዝቡ በማንነቱ፣ በታሪኩ፣በሥልጣኔው ኮርቶ፣አንድነቷ ተጠብቆ፣በእምነቱ ተቻችሎ፣ ሰላሟ ተረጋግጦ፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ሰፍኖና ከድህነት ወጥቶ ለመኖር ያለው ፍላጎት የላቀ ነው። ለዚህም ይተጋል። ያለፈውን ይቅር ማለት ይችልበታል። ዛሬን በሥራዎቹ ውጤትና ነገን ደግሞ በዛሬው ውጤትና በተስፋ ጭምር ይኖራል። ከአባቶቹና ከእናቶቹ የወረሰው የአትንኩኝ ባይነትና የሌሎችን ያለመሻት ባህርይውም ያስመካል። ሕዝቡ ዛሬ በታሪኩ የሚሻውን መሪ አግኝቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የ’’መደመር’’ ሳይንስን ከተለመደው የሂሳብ ቀመር አሳድገው ከፍቅር አሸናፊነት፣ ከይቅርታና ከምህረት አድራጊነት ጋር እያስተማሩን ነው። የአመራሩ ችግሮች፣ በደሎችና ስህተቶች እንደሚታረሙም ሲገልጹ፣ ነገ እንደማይደገሙ ቃል እየገቡ ነው።መሪውና ሕዝቡ አንድ ልብ መሆናቸው በተግባር መታየት ከጀመሩም ሰነባብተዋል። የግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራሮች መስፈን አስፈላጊነትን “ሌብነት’’ን በስሙ በመጥራትም ፀያፍነቱን በመግለጻቸው የሕዝቡን ድጋፍ አግኝተዋል። በየጊዜው በአደባባይ የገቡትን ቃል በገቢር ፈጽመው በማሳየትም ወደር የላቸውም። አመራሩም አገራዊ መሠረቱን እያጠናከረ የወደፊት ትልሙን ሰላምን በማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ ቀፍዳጅና አላሰሩ ያሉ አንዳንድ ዓዋጆች ላይ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው። በመሪው ሀሳብ አመንጪነት እየተከናወኑ ያሉት እነዚህ ተግባራት በአገር ውስጥና በውጭ በሚኖሩ ዜጎች፣ በመንግሥታትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዕውቅና እና ድጋፍ አልተለያቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እያስለመዱት ያለው የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ዘንድሮ ጠንከርና ሰፋ ባለ ሁኔታ ተጀምሯል። ክረምትና በጋ እንዲካሄድም ጥያቄ እየቀረበበት ነው።ወገን ወገኑን የመርዳትና የመደገፍ ባህልን ለማስመለድም የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ጥገናና የድሃ ቤተሰቦች ልጆችን በትምህርት መሣሪያዎች መደገፍ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 2010 ክፉውንም ደጉንም አሳይቶ የራሱን አሻራ ጥሎ አልፏል።ከእንግዲህ ችግሮቻችንን ተነጋግረን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ መፍታት ብቻ ይጠበቅብናል።በዚህም ዳግም ወደ አመጽና አድማ የምንመለስበት ሁኔታ እንደማይፈጠር ተስፋ አለን። አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ እንደምንመኝ ሁሉ፤ በዚያው ልክ መሥራት ከሁላችንም ይጠበቃል። እንደየሙያ ስምሪታችን ለአገርና ለወገን የሚጠቅሙ ሥራዎችን በማከናወን ለውጡን መደገፍና ለተሻለ ሕይወት ተግቶ መሥራት ይጠበቅብናል። በተለይ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት የተሰማሩ ወገኖች የውጭ ምንዛሪ በማፍራት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግና የወገንን ሕይወት በተሻለ ለመቀየር ያስችላል። በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ሥራ የሚፈጥሩ ሀብትና ዕውቀታቸውን ይዘው ቢመጡ፤ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ለአገርና ለወገን ትሩፋት ይሆናሉ።የአገር ልጆች በአገራቸው ልማት ቢሰማሩ ከኪሳራቸው ይልቅ ትርፋቸው እንደሚያመዝን በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል፡፡ ኢህአዴግን ጨምሮ በአገር ውስጥና ከውጭ የገቡት የፖለቲካ ድርጅቶች በ2012 ለሚካሄደው ምርጫ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት አዲስ ዓመት መጥቶላቸዋል። ለነፃ፣ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ ራሳቸውን እያደራጁና እንዲያጠናክሩም 2011 ጊዜ ይሰጣቸዋል። ክልሎችና ኢትዮጵያዊነት:- ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን የምትበቃ አገር መሆኗ ባያጠራጥርም፤ ከማንነት ጋር በተያያዘ በክልሎች እየተስተዋሉ ያሉት ችግሮች ዜጎች ከአንዱ የአገሪቱ ክፍል ወደ ሌላው ተንቀሳቅሰው ለመኖርም ሆነ ለመሥራት አዳጋች ሆኖባቸዋል። ህገ መንግሥቱን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ ክልልሎች እንዳንዶቹ የሌሎችን ተወላጆች ላለማስተናገድ ቆርጠው የተነሱ አስመስሏቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለያየ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተነሱ ግጭቶች ለበርካታ ኣመታት ከኖሩበት፣ ሃብት ንብረት ካፈሩበት አካባቢያቸው ውጡልን ተብለው በሃይል የተፈናቀሉ ዜጎችን በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር በምትተጋ፣ ለአፍሪካ አንድነትና ኅብረት መነሻ በሆነችና ለአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ሞዴልነት ራሷን ለማብቃት ጥረት የምታደርገው አገራችን በውስጥ ችግሮቿ መጠለፍና ለዜጎቿ የማትመች ተብላ መፈረጅ አይገባትም። ይህንንም ያስወገደ የአስተዳደር መዋቅር በመፍጠር ጥንትም፣ ዛሬም ነገም የምንኮራባት አገር እንዳለችን ማሳየት ይገባናል። ራስን በራስ የማስተዳደር መርህ ሳይጣስ ክልልና ማንነትም ሳይጣሉ ሁሉም በሚያሻው መንገድ ተዘዋውሮ የሚሰራባት፣ ያለመሸማቀቅ ወጥቶ የሚገባባት አገር ታስፈልጋናለች። ስደተኞችን ተንከባክባ በምታሳድርና የውጭ ዜጎችን በክብር አስተናግዳ በምትሸኝ አገር ውስጥ እየኖርን ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን መኩሪያ መሆን ሲገባት በአንዳንድ ክልሎች በስጋት የሚወጡባትና የሚገቡባት መሆን አይገባትም። ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር የአገሪቱን አወቃቀር በሚመለከት ዜጎች በክልሎች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ለመኖር፣ ለመሥራትና እየተፈጠሩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ብሎም በጋራ ለምትለማውና ለምትገነባው አገር አንድ ሆኖ ለመቆም የአገሪቱን የመንግሥት አወቃቀር ለሁሉም ዜጎች እንዲመች አድርጎ ማደራጀት ያስፈልጋል። ይህም የወቅቱ ጥያቄ ሆኖ መጥቷል። ከማጠቃለሌ በፊት:- ከሬዲዮ ጋር ያደግኩ ዛሬም በተቻለኝ የማዳምጥ በመሆኔ የአዲስ አበባን ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ስከታተል ዘንድሮ የሰማሁት አንድ ነገር መጪውን ዓመት እንዳስብ ያደርገኛል። በ2010 የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ የአንደኛው ሬዲዮ ጣቢያ ፕሮግራም አቅራቢ ደጋግሞ የሚናገረው ነገር ነበረው። አዲስ ዓመት ገባ ብለን ብዙም ሳናጣጥመው በሌላው አዲስ ዘመን እንደሚተካ። “ባለ ሁለት እግሩ ዓመ አሁን ሲደርስ ታዩታላቸሁ’’ እያለ። እግሮቹ የመጨረሻዎቹን ሁለት አኀዞች ናቸው። ፈጠነም ዘገየም የተባለው 2011 ከፊታችን ቆሟል። አገራችን በባለ ሁለት እግሩ ዘመን ቆማ ሰላሟና አንድነቷ ተጠብቆ ለዜጎቿ የምትመች እንደምትሆን ይጠበቃል። ዜጎቿም “እኔም ለአገሬ!’’ ብለው በወኔና በፍላጎት የጀመሩትን እንቅስቃሴ የሚያሳድጉበት እንደሚሆንም አያጠራጥርም። በሌላኛው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ አንድ ፕሮግራም መሪ ቃል ጽሁፌን ላጠቃልል። “ትልቅ ነበርን፤ትልቅ እንሆናለን!!!’’ ይላል። በእርግጥም ትልቅነታችንን ለቅርብም ለሩቅም፣ ለወዳጅም ለጠላትም የምናሳይበት አዲስ ዘመን መጥቷል። እንቀበለው። እንስራበት። እንለወጥበት። 2010 በቀቢፀ ተስፋ ተሞልተን ከነበርንበት ሁኔታ አውጥቶ ተስፋ ያለው አገርና ሕዝብ መሆናችንን አሳይቶናልና።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም