የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአሳ ሃብትን በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአሳ ሃብትን በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል
ሚያዝያ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአሳ ኃብትን በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል እንደ አማራጭ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።
የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ አገሪቱ ያላትን የአሳ ኃብት ለምግብ ዋስትና ያለው አስተዋጽኦ እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ያላትን የአሳ ኃብት በአግባቡ መጠቀም ከቻለች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያከናወነች ላለው ተግባር አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን አስገንዝበዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ "የውኃ ማማ" እየተባለች የምትጠራው ኢትዮጵያ የአሳ ኃብትን እስከ ቅርብ ጊዜ በአግባቡ እንዳልተጠቀመችበት ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የአሳ ኃብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳታውል ካደረጉ ችግሮች መካከል አንዱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጦት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ችግሩን ለመቅረፍ በዘርፉ ሙያተኞችን እያሰለጠነ መሆኑን ነው የተናገሩት።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፤ በስንዴ ምርት በምግብ እራስን ለመቻል እየተከናወነ እንዳለው ሁሉ ያለውን የውኃ ኃብት በመጠቀም ለአሳ ኃብት ልማትም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ቀጣና የአሳ ኃብት አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር ዋሴ አንተነህም እንዲሁ ኢትዮጵያ በአሳ ኃብት ትልቅ አቅም ቢኖራትም ጥቅም ላይ አላዋለችም ብለዋል።
አገሪቷ በዓመት 94 ሺህ ቶን አሳ የማምረት አቅም ቢኖራትም በአሁኑ ወቅት ግን እየተመረተ ያለው ከ60 ሺህ ቶን በታች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በመሆኑ በዓመት የነፍስ ወከፍ የአሳ አመጋገብ ደረጃም በአማካይ ከግማሽ ኪሎ ግራም እንደማይዘል ጠቅሰው ኢትዮጵያ የአሳ ኃብትን በአግባቡ እየተጠቀመች አለመሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ማሕበረሰቡ አሳን እንደ አንድ የምግብ አማራጭ እንዲጠቀም ግንዛቤ በመፍጠር ዘርፉ ለስራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ሰፊ አማራጭ መጠቀም እንደሚቻል አስረድተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእቅድ ዳሬክተር ተወካይ ወይዘሮ ዘይነብ ናስር በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለአሳ ኃብት ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።
በዚህም በዕቅዱ ውስጥ በአይነት፣ በጥራት፣ በብዛት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል የአሳ ልማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉ በምግብ እራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በተፈጥሮ የተገኘው ላይ ሳይወሰን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።
እንደ ተወካይዋ ገለጻ የህብረተሰቡን የአሳ አመጋገብ ባህል ለማሳደግ ግንዛቤ መፍጠርም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በምስራቅ አፍሪካ አንድ ሰው በአመት በአማካይ 2 ኪሎ ግራም አሳ የሚመገብ ሲሆን ይህም ዓለም ከደረሰበት 21 ኪሎ ግራም ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።