ቀጥታ፡

የእስራኤል የህክምናና የፓርላማ አባላት ቡድን በጎንደር አቀባበል ተደረገለት

ጎንደር ሚያዚያ 4/2014 (ኢዜአ ) የእስራኤል የህክምናና የፓርላማ አባላት የልኡካን ቡድን በጎንደር አጼ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ አቀባበል ተደረገለት፡፡

በልኡካን ቡድኑ የአቀባበል ስነ-ስርአት ላይ ጎንደር ዩኒቨርሲቲና የከተማው አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ ተልአኮ በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም በኩል የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ በቀድሞው የእስራኤል ምክትል የደህንነት ሚኒስትርና በአሁኑ ወቅት የእስራኤል የፓርላማ አባል በሆኑት ጋዲ ባርከን የሚመራ ነው፡፡

ቡድኑ የእስራኤል የፓርላማ አባላትን ጨምሮ የእስራኤል የጤና ተቋማት መሪዎችና የጤና ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል ።

የልኡካን ቡድኑ በሚኖረው የሁለት ቀን  ቆይታ የጎንደር ዩኒቨርሲቲንና የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስራ እንቅስቃሴ ይመለከታል፡፡

ልኡኩ በዛሬው ከቀትር በኋላ ውሎው በጎንደር የሚገኘውን የእስራኤል ቆንስላ ጽህፈት ቤትና በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስት እንደሚጎበኝ ታውቋል፡፡

በነገው እለትም በአማራ ክልል የጤና ተቋማት በወደመባቸው ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ተቋማቱን በህክምና ቁሳቁሶች መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከስራ ሀላፊዎች ጋር እንደሚወያይ ይጠበቃል፡፡

ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ወደ ጎንደር የመጣው ስድስት አባላት ያሉት የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪሞች ቡድን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የህክምና ድጋፍ መስጠት ጀምሯል፡፡

የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቶቹ በሆስፒታሉ ቀዶ ህክምና ለማግኘት ረጅም ቀጠሮ ሲጠባበቁ ለቆዩ ህሙማን ለሶስት ቀን የሚቆይ ነጻ የቀዶ ህክምና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም