የሂዩማን ራይትስ ዎችና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጥናት ሪፖርት በትክክለኛ መረጃ የተደገፈ አይደለም

ሚያዚያ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሂዩማን ራይትስ ዎችና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጥናት ሪፖርት በትክክለኛ መረጃ የተደገፈ አለመሆኑን የባልሲሊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አን ፊትዝ ጄራልድ ተናገሩ።

በቅርቡ ተቋማቱ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በምዕራብ ትግራይ ተከስቷል ያሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የጋራ ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት ሪፖርቱ የፖለቲካ ወገንተኝነትና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የተንጸባረቀበት መሆኑን በመጠቆም ሪፖርቱን እንደማይቀበለው ገልጿል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት በቅርበት የሚከታተሉት ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራልድም የተቋማቱ ሪፖርት ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ሪፖርቱ መሰረታዊ የጥናትና ምርምር አካሄድን የዘነጋና በዋናው የጥናት ክፍልና መደምደሚያ ላይ የተጠቀሱት መረጃዎች እርስ በርሳቸው መመጋገብ የማይችሉ ናቸው።  

በተለይም በማጠቃለያና በምክረ ኃሳብ ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ጥናቱ ዋናው የትንተና ክፍል ውስጥ በዝርዝር ያልቀረቡና ግንጥል ሪፖርት መሆናቸውን ገልጸዋል።     

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ሲካሄድ የፎረንሲክ መረጃዎች የግድ መካተት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ተቋማቱ ጥናትና ሪፖርት ግን ይህንን መሰረታዊ ጉዳይ መዘንጋቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም፤ ጥናቱን ያጠኑት ግለሰቦች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተፈጽሟል ያሉት ሥፍራ ተግኝተው ጥናቱን አለማካሄዳቸውም የጥናት ሪፖርቱ መሉ እንዳይሆን ማድረጉን ተናግረዋል።    

በሌላ በኩል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጉዳዩ ላይ ጥናት አድርጎ ሪፖርቱን ለማቅረብ ሁለት ቀን ሲቀረው ተቋማቱ ሪፖርታቸውን ያቀረቡበት ሁኔታም ፖለቲካዊ ይዘት ሊኖረው እንደሚችል አመላክተዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን እነዚህ ተቋማት ጎንደር ዩኒቨርሲቲን አለማማከራቸው ሌላኛው የጥናትና ምርምር ሥራቸው ጎደሎ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር አን ፊትዝ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የተለያዩ አካባቢዎችን ባለፈው ሣምንት መጎብኘታቸውን ጠቁመው፤ መሰረተ ልማቶች በእጅጉ መውደማቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

በተጓዳኝም በጦርነቱ በርካታ የማኅበሰብ ክፍሎች ችግር ላይ በመውደቃቸው ለዜጎቹ የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ አሁን ካለበት ደረጃ መስፋትና መጠናከር እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የወጡ ረቂቅ ሕጎችም በጦርነቱ የተጎዳውንና ችግር ላይ የወደቀውን ሕዝብ የሚጎዱና ሰብዓዊ ቀውስ እንዲስፋፋ የሚያደርጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም