በጋምቤላ ክልል በመኸር እርሻ ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው--ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በመኸር እርሻ ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው--ቢሮው
ጋምቤላ ሚያዚያ 2/2014 በጋምቤላ ክልል በመኸር እርሻ ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለጸ።
በጋምቤላ ክልል በ2014/15 ምርት ዘመን መኸር ወቅት ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ፣ ማሽላ፣ ሰሊጥና በሌሎች የሰብል ዓይነቶች ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ ለኢዜአ እንደገለጹት አሁን ላይ በምግብ ፍጆታ ምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም በሚያግዝ መልኩ ለመኸር ወቅት የሰብል ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ በ2014/ 2015 ምርት ዘመን በመኸር እርሻ ከ148 ሺህ 780 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች በማልማት ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ተናግረዋል።
በምርት ወቅቱ በሰብል ለመሸፈን የታቀደው መሬት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ35 ሺህ ሄክታር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።
በክልሉ በ50 ሄክታር ማሳ ላይ የቆላ ስንዴ ለማልት በሙከራ ደረጃ ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል'
ከህዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የግብርና ልማት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው ፤ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ለክልሉ አርሶና ከፊል አርብቶ አደር ከ2 ሺህ 170 ኩንታል በላይ የበቆሎ፣ የማሽላ፣ የሰሊጥና ሌሎች የምርጥ ዘር ግብዓቶችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ሃላፊው አስረድተዋል።
የመኸር እርሻ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ በሁሉም ወረዳዎች የእርሻ ትራክተሮች ጨምሮ የአመራርና የባለሙያ ስምሪት በቅርቡ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
አሁን ላይ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር በምግብ ፍጆታ ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ ሁሉም የክልሉ ማህበረሰብ በመኸር የግብርና ልማቱ እንዲረባረብ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
በጋምቤላ ክልል ባለፈው የመኸር እርሻ ከ112 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ማልማት መቻሉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።