የሴቶችን እኩልነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንቅፋት የሚፈጥሩ መዋቅራዊ አሰራሮች ሊሻሻሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን እኩልነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንቅፋት የሚፈጥሩ መዋቅራዊ አሰራሮች ሊሻሻሉ ይገባል
ሚያዚያ 2/2014/ኢዜአ/ የሴቶችን እኩልነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንቅፋት የሚፈጥሩ መዋቅራዊ አሰራሮች ሊሻሻሉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ በፖለቲካው ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ ሴቶችን ለማበረታታት ያለመ "ምስጋና ለጀግኒት" የሚል መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ ምን እንደሚመስል የሚያመላክት ሰነድ ቀርቧል፡፡
ሰነዱን ያቀረቡት ጠበቃና የስርዓተ-ፆታ አማካሪ ወይዘሮ ሰብለ አሰፋ እንዳሉት፤ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ መጎልበት ለመብት ብቻ ሳይሆን ለግለሰብ፣ ለዜጋና ለሀገር የጎላ አስተዋጽኦ አለው፡፡
የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚለካው ወደ ኃላፊነት በመጡ የሴቶች ቁጥር ብዛት ሳይሆን "የስርዓተ ጾታ ጉዳይ ምን ያህል አጀንዳ ሆኗል" በሚለው መስፈርት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ በኋላ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እየጎለበት ቢመጣም ይህ ብቻውን ግብ አይደለም፤ የሴቶች ጉዳይ እንደ ትልቅ አጀንዳ መቀንቀን አለበት ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሴቶች ጫና የሚበዛባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በመሆናቸው በትምህርትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች በመደገፍ ማበረታታት ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለብሔር ብሔረሰቦች የሰጠውን እውቅና ያህል ለሴቶች እኩልነት ትኩረት አለመስጠቱንም ነው ያብራሩት፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢዜማ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ሴቶች የጥንካሬያችን ምልክቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ኢዜማ በተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ወቅት ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች ሲገጥሙት ችግሮችን ያለፈው በሴቶች ጥንካሬና ብርታት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ግማሽ ያህሉ ሴቶች ቢሆኑም ያላቸው ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማሳደግ በሀገራቸው ጉዳይ ከወንዶች እኩል የወሳኝነት ሚና እንዲኖራቸው ህገ-መንግስቱን ጨምሮ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የሴቶችን እኩልነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንቅፋት የሚፈጥሩ መዋቅራዊ አሰራሮች ሊሻሻሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡