ቀጥታ፡

ኬንያ 'ብሉ ኢኮኖሚ'ን በዘላቂነት ለመጠቀም ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ትፈልጋለች

ሚያዚያ 2/2014/ኢዜአ/ ኬንያ 'ብሉ ኢኮኖሚ'ን ዘላቂነት ባለው መልኩ ለኢኮኖሚ እድገት ለማዋል ከኢትዮጵያ ጋር መሰራት እንደምትፈልግ ገለጸች።

'ብሉ ኢኮኖሚ' በሀይቅ፣ ውቅያኖስና ሌሎች ከውኃ ጋር ተያየዥነት ባላቸው ምጣኔ ኃብታዊ ዘርፎችን በዘላቂነት መጠቀም ላይ የሚያተኩር ነው።

አፍሪካ ከዚህ ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልበት እምቅ አቅም እንዳለም ጥናቶች ያመላክታሉ።

በምስራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ኬንያ 'ብሉ ኢኮኖሚ'ን በቱሪዝም ዘርፍ በመጠቀም የተሻለ ልምድ እንዳላት ተመልክቷል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይን መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ባወጣው መረጃ መሰረት የቀጣናው የቱሪዝም ዘርፍ 'ብሉ ኢኮኖሚ' ከሚያመነጨው 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 75 በመቶው የኬንያ ድርሻ ነው።

የኬንያ 'ብሉ ኢኮኖሚ' ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ፍራንሲስ ኦዊኖ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በዘርፉ ያለውን ሃብት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች ጋር በትብብር መጠቀም ትፈልጋለች ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ታሪካዊ ስፍራዎች፣ አስገራሚ ተፈጥሮና ሌሎች መስህቦች ካላቸው አገሮች አንዷ መሆኗን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ለማስፋት እያደረገ ያለው ጥረትም ለ'ብሉ ኢኮኖሚ' ዘርፍ እድገት ተጨማሪ እሴት እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ዓለም አቀፍ ማሪታይም ህግ ባለሙያ አነኔ ቀጀላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ በ'ብሉ ኢኮኖሚ' ዘርፍ መስራት ከጀመረች አጭር ጊዜ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአሳ ማስገር፣ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት፣ ወደብ ግንባታ፣ በኤሌክትሪክ ሀይልና በሌሎች ዘርፎች ከምስራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል።

አፍሪካ ከ'ብሉ ኢኮኖሚ' 2 መቶ 96 ቢሊዮን ዶላር የምታገኝ ሲሆን ለ49 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።

እ.አ.አ. በ2030 ዓ.ም ደግሞ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከ4 መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስና ለ57 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን የአፍሪካ ሕብረት መረጃ ያሳያል።

በዘላቂ ልማት ግቦች ከተቀመጡ 17 ግቦች አንዱ ለ'ብሉ ኢኮኖሚ' ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን ዘርፉን ለዜጎች ብልጽግና እና ዘላቂ ዕድገት አካታችነት ባለው መልኩ መጠቀም እንዲቻል ያስቀምጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም