ሠራዊቱ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የበጎ አድራጎት ስራዎችን ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የበጎ አድራጎት ስራዎችን ጀመረ
ነሃሴ 30/12/2010 የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት አዲሱን ዓመት በሁሉም የሠራዊቱ ክፍሎች የበጎ አድራጎት ስራዎችን በማከናወን ለመቀበል እንቅስቃሴ መጀመሩን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክቶሬት ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ተሰማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን የበጎ አድራጎት ጥሪ ተከትሎ ሰራዊቱ አረጋዊያንን፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞችን በመርዳትና በመደገፍ ነው አገራዊ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ የጀመረው። በዚህም ሰራዊቱ ለአገራዊ ንቅናቄው አካል በመሆን ያለውን አካፍሎ በመስጠት፣ ለተቸገሩ ፈጥኖ በመድረስና ሁልጊዜም እውነተኛ የሕዝብ ልጅ መሆኑን ዳግም በተግባር በማስመስከር አዲሱን ዓመት ለመቀበል ተዘጋጅቷል ነው ያሉት። ሰራዊቱ ከዚህ ቀደም ለህጻናት፣ አቅመ ደካማ፣ አረጋዊያንና የተፈጥሮ አደጋ ላጋጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ አሁንም በተደራጀ መንገድ የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ በተቋሙ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ነው ያሉት። ሁልጊዜም ህዝባዊነት በማስቀድም ተልዕኳቸውን በላቀ ደረጃ እየተወጡ የሚገኙት የአገር መከላከያ ሰራዊት በየግዳጁ ቀጠናዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ችግሮችን የመለየት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ሰራዊት አባላት የመልካም አዲስ ዓመት ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።