የታሪክ ጸሐፊዎች የኢዜአን የ80 ዓመታት መረጃዎች ለታሪክ ምንጭነት ሊጠቀሙበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የታሪክ ጸሐፊዎች የኢዜአን የ80 ዓመታት መረጃዎች ለታሪክ ምንጭነት ሊጠቀሙበት ይገባል
ሚያዝያ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፉት 80 ዓመታት መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግና ኢትዮጵያውያንን በማቀራረብ ያደረገውን ጥረት የታሪክ ምሁራን በታሪክ ምንጭነት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አውደ ርዕይውን የጎበኙ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ተናገሩ።
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህሩ ዶክተር ተሻገር ሀብቴ እንደገለጹት፤ ኢዜአ በመረጃው ኢትዮጵያውያንን አቀራርቧል፤ በታሪክ ይሄን ያደረጉ የድርጅቱ መሪዎች ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በባህር ዳር ከተማ ለሦስት ቀናት የተዘጋጀው የተቋሙን የ80 ዓመታት ጉዞ የሚያሳየው የቪዲዮና ፎቶ አውደ ርዕይ ዛሬ ተጠናቋል።
ለሦስት ቀናት የቆየውንና የድርጅቱን የ80 ዓመታት ጉዞ የሚያሳየው የቪዲዮና ፎቶ አውደ ርዕይ በባህርዳር ከተማ የሚገኙ በርካታ የኅብረተስብ ክፍሎች ጎብኝተውታል።
ላለፉት 80 ዓመታት ተሠርተው በየመገናኛ ብዙሃኑ የተሰራጩት የኢዜአ መረጃዎች የታሪክ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸውን ያነሱት ምሁሩ፤ የታሪክ ፀሐፊዎች እነዚህን መረጃዎች በታሪክ ምንጭነት ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያዘጋጀው አውደ ርዕይ የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ትናንትና ዛሬን እንድንረዳ አስችሎናል ብለዋል።
አውደ ርዕይውን የጎበኙት ከከተማው ዙሪያ የመጡ ተማሪዎች በበኩላቸው በከተማቸው የተከፈተው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) የ80 ዓመታት ጉዞ የሚያሳየው የቪዲዮና ፎቶ አውደ ርዕይ ስለ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው ገልጸዋል።
ኢዜአና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ትናንት የት እንደነበሩ ዛሬ ደግሞ እንዴት እየሠሩ እንደሚገኙ ከአውደ ርዕይው ለመገንዘብ እንደቻሉ አስረድተዋል።
አውደ ርዕይውን የጎበኙት በሀገር መከላከያ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ባልደረቦች እና የባህርዳር ከተማ ፖሊስ ባልደረቦች በበኩላቸው፤ ኢዜአ ሚዛናዊ የመረጃ ምንጭ በመሆን ላለፉት 80 ዓመታት የዘለቀበት መንገድ ለሌሎች ተቋማት በአርአያነት ሊያስጠቅሰው የሚችል መሆኑን ጠቁመው፤ አንጋፋነቱን በአግባቡ የሚገልጹ ተጨማሪ የድምጽና የተንቀሳቃሽ ምስሎች ቢጨመሩ መልካም ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተቋማት ታሪክ ለ80 ዓመታት ታሪካዊ ሂደታቸውንና ስያሜያቸውን ጠብቀው ከቆዩ ጥቂት ተቋማት መካከል ኢዜአ አንዱ ነው ያሉት የባህርዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ተገኝ ወርቁ፤ ኢዜአ እንዳንጋፋነቱ አሁን እየሰጠ ያለውን የመረጃ ምንጭነት ይበልጥ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊ፣ ሕዝባዊ ሆኖ መሥራት ላይ ሊተጋ ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።
በባህርዳር ከተማ ከመጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ ላለፉት ሦስት ቀናት የተካሄደው አውደ ርዕይ ዛሬ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ/ም ተጠናቋል።