ሌብነትና ብልሹ አሰራር በኢትዮጵያ ቁልፍ ማህበራዊ ችግር እየሆነ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ሌብነትና ብልሹ አሰራር በኢትዮጵያ ቁልፍ ማህበራዊ ችግር እየሆነ መጥቷል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2014(ኢዜአ) ሌብነትና ብልሹ አሰራር በኢትዮጵያ ቁልፍ ማህበራዊ ችግር እየሆነ መምጣቱን የፌዴራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡
በኮሚሽኑ የማቴሪያል ዝግጅትና የስነ-ምግባር ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አክሊሉ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ሌብነት እንደ አገር የስጋት ደረጃው እየጨመረ መጥቷል፡፡
ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት ሙስና ከማህበራዊ ችግሮች ውስጥ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ በቅርቡ በተካሄደ ጥናት ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ሶስተኛው ማህበራዊ ችግር መሆኑ ተረጋግጧልብለዋል::
ይህም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን ያህል እየተባባሰ መምጣቱን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መታገል ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም በኃላፊነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ተቋማት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ስርዓት መገንባት ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አንስተው፤ ሌብነትን የሚጠየፍ ትውልድ መፍጠር ደግሞ የችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ባከናወናቸው ተግባራት በቢሊዮን የሚቆጠር የተመዘበረ ገንዘብ እንዲመለስ እና ሙሰኞች በህግ እንዲጠየቁ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ይህም ከችግሩ ስፋት አኳያ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ አሁን ላይ ሌብነትን የመከላከል ስራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ሌብነትን መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠቱ ይታወቃል፡፡