ቀጥታ፡

በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 6 ሺህ 600 ሊትር ቤንዚን ከነተጠርጣሪዎቹ ተያዘ

ሶዶ፣ ሚያዚያ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 6 ሺህ 600 ሊትር ቤንዚን ከነተጠርጣሪዎቹ ጋር ዛሬ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረውን ቤንዚን መቆጣጠር መቻሉን የገለጹት የዳሞት ጋሌ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር መንበረ ዶይሶ፤ የቤንዚኑ መነሻ ሻሸመኔ ከተማ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3ቢ-22834 አ.አ የደረቅ ጭነት አይሱዙ ተሽከርካሪ መድረሻውን ጋሞ ዞን ሰላምበር ከተማ ለማድረግ ታስቦ ሲጓዝ ከህብረሰተብ በደረሰ ጥቆማ መሰረት  የጸጥታ ሃይሎች ባደረጉት ክትትል መቆጣጠር እንደተቻለም አስረድተዋል።  

ከጉዳዩ በጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታወቀዋል።

ቤንዚንና ሌሎችም በድጎማ የሚገቡ ምርቶች ላይ የሚደረግ ስርቆትና ህገ ወጥ ንግድ ህዝብና ሀገርን  ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳርግ መሆኑን ያነሱት ኢንስፔክተር መንበረ፤  ህብረተሰቡ ህገወጦችን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል በመግለጽ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም