እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥራዎች ኢትዮጵያዊነትን የሚያንፀባርቁና ለስነ-ጥበባዊ ሂስ የተመቹ ናቸው

ሚያዚያ 1/2014 (ኢዜአ) እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የሥዕል ሥራዎች ኢትጵያዊነትን የሚያንፀባርቁና ለስነ-ጥበባዊ ሂስ የተመቹ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ።

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአረፉበት 10ኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ በሳይንስ አካዳሚ የተከፈተው አውደ ርዕይ ትናንት የተጀመረ ሚያዚያ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

ሰዓሊው በኢትዮጵያና በአውሮፓ ለረጅም ዓመታት የሥነ ጥበብ ሙያን የተማሩና በአገር ውስጥ ይሁን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የሥዕል አውደ ርዕዮችን ማቅረብ ችለው ነበር።

በዚህ ልዩ ተስጥዖቸውና ችሎታቸው የተነሳም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከሚገኙ ታላላቅ የጥበብ ሰዎች ጋር ለመገናኘትና ሥራዎቻቸውን ለሌሎች ለማሳወቅ ችለዋል።

በሥነ-ጥበብ ሥራዎቻቸውም ለዓለማችን ሰላምን፣ ለሰው ልጆች አንድነትና እኩልነትን በተለይም ኢትዮጵያዊነትን መስበክ እንደቻሉም ይነገርላቸዋል።

ይህም በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ሰዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር ለመገናኘትና ዓለማቀፋዊ ዝናን እና ክብርን እንዲያተርፉ እንዳስቻላቸውም እንዲሁ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ'አለ' የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሠዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን፤ የአርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ሥራዎች ለኢትዮጵያዊ ሥነጥበብ ትልቅ ግምት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

በሥዕል ሥራዎቻቸውም ላይ ኢትዮጵዊ የአሳሳል ቴክኒኮችን ከዘመናዊ አሳሳል ጋር አዋህደው ማቅረብ ችለው እንደነበርም መስክረውላቸዋል።

ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ ደግሞ የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥራዎች ኢትዮጵያዊ ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ የተመሰረቱና የቤተክህነት ጥንታዊ አሳሳልን ከዘመናዊው ጋር ያስተሳሰሩ ናቸው ይላሉ።

ሰዓሊው በውጪ ሀገር የተማሯቸው ትምህርት ተፅዕኖ ሳያሳድሩባቸውም ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ላይ ተመስርተው ሥዕሎቻቸውን ሲሰሩ እንደነበርም አክለዋል።

በሌላ በኩል የሠዓሊው ሥራዎች ለዕይታና ለውይይት መቅረብ በኢትዮጵያ የሌለውን የኪነ-ሂስ ባህል ለማነቃቃት እንደሚረዳ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ሠዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን ''የማይፃፍበትና ውይይት የማይደረግበት የሥነ-ጥበብ  ሥራ ሊታወቅ አይችልም'' ይላሉ።

የጥበብ ስራዎች የበለጠ እንዲያድጉና እንዲጎለብቱ ከዚህ በኃላ ለኪነጥበብ ሂስ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ በበኩላቸው ሂስ ትልቅ ዕውቀትን የሚጠይቅ መሆኑንና ኪነጥበብ ውስጥ ያለን ፍልስፍና አውጥቶ የሚያሳይ  ነው ብሏል።

የኪነ ጥበብ ሂስ ራሱን የቻለ እውቀት በመሆኑ ሊሰራበት እንደሚገባም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም