ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሰላምና ልማት ጠንክረን እንሰራለን- የሊጉ አባላት

ጋምቤላ፤ ሚያዚያ 1/2014(ኢዜአ) የብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ወጣቶች ሊግ አባላት ሌብነትን አምርሮ በመታገል ለክልላቸው ብሎም ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና ልማት ጠንክረው ለመስራት ቃል ገቡ።

የሊጉ አባላት የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ  ጉባኤ በተላለፈው ውሳኔዎች ዙሪያ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ያደረጉትን ውይይት ሲያጠናቅቁ ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫ ነው ቃል የገቡት።

ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውንና ወንድማማችነትን በማጎልበት ከውስጥም ሆነ ከውጪም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል ለመሻገር ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

አሁን ላይ የኑሮ ውድነት በማባባስ ህዝቡን እያማረሩ ያሉትን ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን በማጋለጥ ረገድም የበኩላቸውን ለመወጣት ዝጁነታቸውን በአቋም መግለጫቸው አረጋግጠዋል።

ሌብነትና የተደራጀ ስርቆትን አምርሮ በመታገል  ለክልላቸው ብሎም ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና ልማት ጠንክረው እንደሚሰሩ በጋራ በገቡት  ቃል ገልጸዋል።

በብልጽግና አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ለተላለፉ ውሳኔዎች ስኬታማነት የክልሉ ወጣቶች በትጋት ሊሰሩ ይገባል ያለችው ደግሞ  የፓርቲው የወጣቶች ሊግ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወጣት አባንግ ኮመዳን ናት።

የኑሮ ውድነት ለማርገብ ወጣቱ ያለውን እውቀትና አፍላ ጉልበት አቀናጅቶ በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የተናገረው ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ስራ አስፈፃሜ አባል ወጣት አክሊል ዓለሙ ነው።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ራች ባየክ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር እያጋጠሙ ያሉትን ፈተናዎች በድል ለመሻገር በሚደረገው ጥረት ከወጣቱ ኃይል የላቀ ሚና ይጠበቃል ብለዋል።

በተለይም የሌብነት፣ የጽንፈኝነትና የጎሰኝነት አመለካከት  አምርሮ በመታገል ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማትም እንዲሁ።

ውይይቱ የተካሄደው "የፈተናዎች መብዛት የብልጽግና ጉዟችንን አያስቆመንም ’’ በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም