ቀጥታ፡

በጦርነትና በድርቅ ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጦርነትና በድርቅ ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች እየተደረገ ስላለው የጤና አገልግሎት መግለጫ ሰጥተዋል።

በጦርነትና በድርቅ ምክንያት በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች የስነ-ልቦና ማማከርን ጨምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ በዚሁ ጉዳይ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በአፋር ክልል በአምስት ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር በ16 መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ 249 ሺህ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍን ጨምሮ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአማራ ክልልም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸው፤ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ 40 የመጠለያ ጣቢያዎች 53 ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖች ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ለ130 ሺህ ዜጎች የወሊድና የጤና አገልግሎት እንዲሁም ለ10 ሺህ ዜጎች የአእምሮና የስነ-ልቦና ህክምና መሰጠቱንም ዶክተር ደረጀ ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በደቡብ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንድ ዞን ድርቅ መከሰቱን አስታውሰዋል።

በመሆኑም በርካታ ዜጎችን ለከፍተኛ ችግር ከመዳረጉ ባሻገር ለእንስሳት ሞትና ለሰዎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በመሆኑም የዜጎችን ህይወት ለመታደግ የአልሚ ምግብ አቅርቦትና የጤና አገልግሎት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክትባትና መሰል አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ቡድኖች ተቋቁመው እየሰሩ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በሶማሌ ክልል ለ193 ሺህ ዜጎችና በኦሮሚያ ክልል ለ424 ሺህ ዜጎች የኮሌራና የኩፍኝ ክትባት መሰጠቱንም አስታውሰዋል።

በድርቅ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች 14 በመቶ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የአልሚ ምግብ በተጨማሪ በህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ወቅት ከወደሙ የጤና ተቋማት በርካቶቹ ዳግም ተደራጅተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም