በጎዳና ላይ የሚኖሩ ወገኖችን የማንሳትና መልሶ የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ቢሆንም ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ ዘላቂ መፍትሄ ይሻል - ኢዜአ አማርኛ
በጎዳና ላይ የሚኖሩ ወገኖችን የማንሳትና መልሶ የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ቢሆንም ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ ዘላቂ መፍትሄ ይሻል
ሚያዚያ 1/2014 (ኢዜአ) በጎዳና ላይ የሚኖሩ ወገኖችን የማንሳትና መልሶ የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ቢሆንም ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ ዘላቂ መፍትሄ የሚሻ መሆኑን የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
በዘንድሮው ዓመት ከ14 ሺህ በላይ ዜጎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት የስልጠና እና ድጋፍ አገልግሎት መደረጉም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገነት ቅጣው፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ዜጎችን ከጎዳና ላይ የማንሳት ስራ እየተከናወነ ቢሆንም ፍልሰቱ መቆም ባለመቻሉ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል።
በዘንድሮ ዓመት ከ14 ሺህ በላይ ዜጎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት የስልጠና እና ድጋፍ ሲደረግ ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ፍላጎት ያላቸውን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በገፊ ምክንያቶች ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከ26 የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዜጎችን ከጎዳና ላይ የማንሳትና በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በጎዳና ላይ የሚኖሩ ወገኖችን የማንሳትና መልሶ የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ቢሆንም ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ ዘላቂ መፍትሄ ይሻል ብለዋል።
በዚሁ ተግባር ላይ እገዛ እያደረገ የሚገኘው የተስፋ ለህጻናት ግብረሰናይ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ማሙዬ፤ ወገኖችን ከጎዳና ላይ የማንሳት ተግባር እየተከናወነ ቢሆንም ገፊ ምክንያቶችን በመለየት ለዘላቂ መፍትሄ መስራት ይገባል ብለዋል።
በማእከሉ ከጎዳና ተነስተው ስልጠና በመውሰድ ላይ ካሉት መካከል ወይዘሮ አስቴር ታሪኩ ከከፋ የጎዳና ህይወት ተነስተው ስልጠና እየወሰዱ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
''ከጎዳና ህይወት ወጥቼ የልብስ ስፌት ስልጠና እየወሰድኩ ነው ከስልጠና በኋላ የኔና የልጄን ሕይወት እቀይራለሁ የሚል ተስፋ ሰንቄያለሁ'' ብለዋል።
በተደረገላት ድጋፍ ከጎዳና ህይወት ወጥታ የራሷን ስራ በመጀመር በኑሮዋ መለወጧን የምትናገረው ደግሞ ወጣት ሊዲያ ከድር ነች።