በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል
ሚያዚያ 1/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ችግር ቅድሚያና አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ/ኢሕአፓ/ ገለፀ።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ /ኢሕአፓ/ 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን "ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ለዴሞክራሲና የህግ የበላይነት እንታገላለን" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።
የፓርቲው መሪ አቶ ገብረወልድ ወልደሰንበት፤ በንግግራቸው በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ የተፈናቀሉና ለከፋ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራም የተለየ ትኩረት ይሻል ነው ያሉት።
በአሸባሪው የህወሃት ቡድን በከፈተው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የአፋርና አማራ ክልሎች መልሶ ከመገንባት አኳያም የጋራ ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ፤ ፓርቲው የዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታን ለማስፈን በርካታ ልጆቹ መስዋትነት መክፈላቸውን ጠቅሰዋል።
''በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ እዚህ የደረሰው ፓርቲው የፖለቲካ ጽናቱ ለሌሎች ተፎካካሪዎች ፓርቲዎች ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል አድርጓል'' ሲሉም ተናግረዋል።
"በአሁኑ ወቅት ሀገርን ለመለወጥ በመተባበርና መደማመጥ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ትግልን መከተል እንደሚገባም ዶክተር ራሔል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፤ ኢሕአፓ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የሚገጥሙትን ፈተናዎች በብቃትና በጥንካሬ በመወጣት ጉልህ የፖለቲካ የትግል ታሪክ ያለው ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ‘ኢሕአፖ' በ1964 ዓ.ም የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።