በሉዓላዊ አገር ላይ የሚጣል ማዕቀብ ህዝብን ለከፋ ችግር እና ስቃይ የሚዳርግ የጭካኔ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሉዓላዊ አገር ላይ የሚጣል ማዕቀብ ህዝብን ለከፋ ችግር እና ስቃይ የሚዳርግ የጭካኔ ተግባር ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሃያላን አገሮች በአንድ ሉዓላዊ አገር ላይ የሚጥሉት ማዕቀብ ህዝብን ለከፋ ችግር እና ስቃይ የሚዳርግ የጭካኔ ተግባር ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሆርጌ ለፌብሬ ኒኮላስ ተናገሩ።
በማንኛውም ሉዓላዊ አገር ላይ ማዕቀብ በማሳረፍ ብዙሃኑን ህዝብ ተጎጂ ከማድረግ አስቀድሞ ችግሮችን ለመፍታት የዲፕሎማሲ ጥረት ትልቅ ሥፍራ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
አምባሳደር ሆርጌ ለፌብሬ ኒኮላስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኃያላን አገራት በሌሎች ላይ ያልተገባ ማዕቀብ በመጣል ህዝብን ለከፋ ችግርና ስቃይ እየዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕቀብ አድራጊዎቹ "የህዝቡን ህይወት ለማሻሻል ነው" የሚል መልእክት እያስተላለፉ ቢሆንም ብዙሃኑን ህዝብ በተጨባጭ ለስቃይና ችግር እየዳረጉት መሆኑን ገልጸዋል።
"ብዙሃኑን ህዝብ በረሃብ እየቀጡ የፖለቲካ ግብ ማሳካት አይቻልም" ያሉት አምባሳደሩ በአንድ ሉዓላዊት አገር ላይ የሚጣል ማዕቀብ ህዝብን ለከፋ ችግር እና ስቃይ የሚዳርግ የጭካኔ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት የራሳቸውን የዴሞክራሲ አካሄድ ለሁሉም ሀገራት ለክተው መስጠት ስለሚፈልጉ ሌሎች ሀገራት በራሳቸው መንገድ ዴሞክራሲን እንዲለማመዱ የማይፈቅድ አካሄድ ነው ብለዋል።
በሉዓላዊ ሀገራት ጣልቃ እየገቡ ያልተመቿቸውን መንግስታት ለመለወጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አውግዘዋል።
አገራት የራሳቸው ችግር ሊኖራቸው ይችላል፤ ሁሉም አገሮች ግን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ጽኑ እምነት እንዳላቸውም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የምዕራቡ ዓለም አገራት በእርግጥም ለሕዝብ መብትና የተሻለ ሕይወት የሚቆሙ ከሆነ ሀገራት ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም እንዲፈቱ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የኃያላን አገራት ትኩረት ከዲፕሎማሲ ይልቅ በማዕቀብ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ለህዝብ የመፍትሄ አማራጭ ከመሆን ይልቅ የችግርና ስቃይ መንስኤ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
ከማዕቀብ ይልቅ የዲፕሎማሲ ጥረትን ማስቀደም ልዩነቶችን ለመፍታትና የህዝብን ሰላምና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ቀዳሚ ተመራጭ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እና ኩባ የረዥም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸው አገሮች ሲሆኑ፤ ከ44 ዓመታት በፊት የዚያድባሬ ወታደራዊ ኃይል በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሲፈጽም የኩባ መንግስት ለኢትዮጵያ ነጻነት የሚታገሉ ወታደሮችን መላኩ ይታወቃል።