ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
ሰቆጣ ፤ ሚያዚያ 01/2014 (ኢዜአ) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
በዩኒቨርሲቲው የአስራት ወልደየስ ጤና ሳይንስ ካምፓስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶከተር ቴዎድሮስ ክፍለዮሐንስ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው በህወሓት ወረራ በተለያዩ አካባቢዎች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን እየደገፈ ነው።
በዛሬው እለትም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብ እህልና የፍራሽ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
"ከድጋፉ ውስጥም 700 ኩንታል የስንዴ እና የጤፍ ዱቄት፣ 100 ኩንታል ሩዝ እና 209 ፍራሾች ይገኙበታል" ብለዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቄያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ ድረስም ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የዋግ ኽምራ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ጥላሁን አምበሉ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር በጊዜያዊነት የሚያቃልል ነው።
በተመሳሳይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለእነዚህ ተፈናቃዮች 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ትናንት ማድረጉ ታውቋል።