ቀጥታ፡

በአርቲስት አፈወርቅ ተክሌ 10ኛ ዓመት የእረፍት መታሰቢያን በማስመልከት የሥዕል አውደ ርዕይ ተከፈተ

መጋቢት 30/2014/ኢዜአ/ እጅግ በጣም የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ 10ኛ ዓመት የእረፍት መታሰቢያ በማስመልከት በሳይንስ አካዳሚ የሥዕል አውደ ርዕይ ተከፈተ ።

የሥዕል አውደ-ርዕዩ ከዛሬ መጋቢት 30/2014 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 8/2014 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የአርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የሥዕል ሥራዎች ይቀርባሉ ተብሏል።

በሠዓሊው ሥራዎች ላይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር በሠዓሊ በቀለ መኮንንና በደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ የኪነ-ሂስ ዝግጅት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የሥዕል አውደ ርዕይ የተከፈተው በሥዕል ላይ ያለው የኪነ-ሂስ ባህል እንዲዳብር መሆኑን ገልፀዋል።

"ያለንበት ዘመን ከፍተኛ የማንነት ጥያቄ ውስጥ የገባንበት ነው" ያሉት የአካዳሚው ፕሬዘዳንት የሠዓሊው ሥራዎች ኢትዮጵያዊነታችንን እንድናውቅ ከፍተኛ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሠዓሊ በቀለ መኮንን የአርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥራዎች ትልቅ የጥበብ ልህቀት የሚታይበት ነው ብሏል።

ዛሬ የተከፈተው የሥዕል አውደ-ርዕይ የአርቲስቱ የሥዕል ሥራዎች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ በብዛት ለዕይታ የቀረቡበት እንደሆነም ገልጿል።

ይሄ ደግሞ በሥነ-ጥበብ ውስጥ ካሉ ሰዎች በስተቀር በጥልቀት የማያውቋቸውን የሠዓሊውን ሥራዎች ኅብረተሰቡ እንዲያውቃቸው ዕድል ይፈጥራል ነው ያለው።

በአካዳሚውም የቀረቡት የአርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥራዎች ከተማሪነታቸው ጀምሮ በሙያ ሕይወታቸው ውስጥ የሰሯቸውን ስለሚያካትት የሥራዎቻቸውን ዘዬና አቅጣጫዎች ለማየት እንደሚያስችልም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም