ቀጥታ፡

ባለሀብቱና የንግድ ማህበረሰብ ለአምራች ኢንደስትሪው ዘርፍ እድገት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ተጠየቁ

ሀዋሳ መጋቢት 30/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት የኢኮኖሚ ጫና እንድትወጣ የግል ባለሀብቱና የንግዱ ማህበረሰብ ለአምራች ኢንደስትሪው ዘርፍ እድገት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ተጠየቀ።

የሲዳማ ክልል የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በሀዋሳ ከተማ  ተካሂዷል።

በፎረሙ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሶ እንዳመለከቱት፤ ኢትዮጵያ የውስጥና የውጪ ተጽዕኖ ለመቋቋም በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ በማተኮር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ጥረቱ መጠናከር አለበት ።

"ለአምራች ኢንዱስትሪው ውጤታማነት ማነቆ የሆኑ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግሮችን ከማስወገድ ባሻገር በአተገባበር ሂደት የተለዩ የህግና የአሰራር ክፍተቶችን ለይቶ በማሻሻል ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት መሰራት አለበት" ብለዋል።

ሀገሪቱ ድህነትን በማስወገድ ወደ ብልጽግና ለመጓዝ ለያዘችው ራዕይ ስኬታማነት ባለሀብቱና የንግዱ ማህበረሰብ የተሰማራበትን ዘርፍ በማሳደግ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪ ላይ አተኩሮ  እንዲሰራ ጠይቀዋል።

አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በርካታ የሰው ኃይል የሚቀበል እንደመሆኑ ስራ አጥነት በመቀነስ ባለሀብቱ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አሳስበዋል።

በአገልግሎት ዘርፍና በመሰረተ ልማት አቅርቦት በተለይ በውሀ፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎትና ብድር አቅርቦት ዙሪያ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት እንዲሰሩ  አስገንዝበዋል።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሩ፤  በክልሉ በገጸምድርና ከርሰ ምድር ያለውን ከፍተኛ እምቅ ሀብት በማልማት የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ባለሀብቱ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አተኩሮ ወደ ስራ ሊገባ ይገባል ነው ያሉት።

በክልሉ ከዚህ ቀደም ከ2 ሺህ በላይ ባለሀብቶች በተለያዩ መስኮች በመሰማራት ስራ መፍጠራቸውን አስታውሰዋል።

በክልሉ በተገቢው መንገድ ስራቸውን የሚሰሩ ባለሀብቶች እንዳሉ ሁሉ፤ የተረከቡትን ቦታ አጥረው ወደ ስራ ያልገቡትን በመለየት ቢሮው እርምጃ እንደሚወስድ አሰታውቀዋል።

ሀገሪቱ በውጭ ኃይሎች ከሚደርሰባት ተጽዕኖ ለመላቀቅ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማገዝ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በፎረሙ ላይ በክልሉ በተሰማሩበት የኢንቨስትመንት መስክ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ባለሀብቶች የምስክር ወረቀት፣ሜዳልያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም