የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እዳ ያለባቸው ተቋማት እዳቸውን ከፍለው ከኪሳራ እንዲወጡ መሥራት አለበት

110

መጋቢት 30/2014 (ኢዜአ) የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በሥሩ ያሉ እዳ ያለባቸው ተቋማት እዳቸውን ከፍሎ ከኪሳራ እንዲወጡ በትኩረት መሥራት እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አሳሰበ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደርን በመስክ ጉብኝት ምልከታ አድርጓል።

በዚሁ ወቅት ቋሚ ኮሚቴው አስተዳደሩ በመንግሥትና በውጭ እዳ ብድር መክፍል ያልቻሉ በሥሩ የሚገኙ ተቋማት ዕዳቸውን እንዲከፍሉ አሳስቧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ካለው ትልቅ አገራዊ ፋይዳ አንጻር በሥሩ የሚገኙ የተወሱ ተቋማት ከኪሳራ እንዲወጡ ሊሰራ ይገባል።

ለአብነትም የኢትዮ-ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ውይም የድሮ ሜቴክ፣ የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት ፋብሪካ ከኪሳራ እንዲወጡ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ብድር ያለባቸውና ለኪሰራ የተዳረጉ እንደ የያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የኬሚካል ኢንደስትሪዎች ላይም በቀጣይ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች የሚያነሱትን የጥቅማጥቅምና የደሞዝ ጥያቄ ሊፈታላቸው ይገባልም ሲሉም አሳስቧል።

በከፍተኛ ሁኔታ በየተቋማቱ የተከማቹት ንብረቶች፣ ማሽነሪዎች፣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ትልቅ ዋጋ ያላቸው ሃብቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስቧል።

የተገኙ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮችም ለመፍታት መሥራት ይኖርብታልም ብለዋል።

የልማት ባንክን ካለበት ችግር ለማላቀቅ የተሰራው ሥራም አበረታች መሆኑንም ተናግረዋል።

የሰነዶች አያያዝና አደረጃጀት፣ የተቋሙ የሪፎርም ሥራ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የተሰሩት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውም ገልጸዋል።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሃብታሙ ኃይለሚካሄል በበኩላቸው አስተዳደሩ ከለውጡ በፊት ከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበሩ በርካታ ድርጅቶች እንደነበሩ ገልጸው እሱን ለመፍታት በተሰራው ሥራ ጥሩ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የተወሰኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ብድርና ውስጥ የተዘፈቁ እንደነበሩ ገልጸዋል።

ለአብነትም ኢትዮ-ኢንጅነሪነግ/ሜቴክ ምንም አይነት የፋይናንስ ሥርዓት ያልተከለ ከፍተኛ ጉደለት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በተቋሙ ላይ በተሰራው ሥራ ከ12 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያልአግባብ የተቀጠሩ ከድርጅቱ እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል።

የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበትም ገልጸው ጥፋቱን ያደረሱ ሰዎች ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንና ሌሎችንም ተቋማት የገቡበትን ችግር ለመፍታት በጥናት የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠትና ወደ ግል የሚዞሩትን ለማዞር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምዝበራ፣ የሃብት ብክነትንና ሌብነትን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር የመዘርጋት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ከባለፈው ችግር አንጻር መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸው የአሰራር ሥርዓት የመዘርጋት ሥራ በመሥራት የተሻላ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተጠቀሱት ተቋማት ውጭ ሌሎች ተቋማት በጥሩ አፈጻጸም ላይ ያሉና ለመንግሥትም ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በሥሩ 36 የመንግሥት ተቋማት ያሉ ሲሆን ከ1983 ዓ.ም እስከ አሁን ከ300 በላይ ተቋማት ወደ ግል ይዞታነት ዞሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም