ቀጥታ፡

ኢዜአ በአፍሪካ አስተማማኝና ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ሆኖ እንዲወጣ እየተሰራ ነው

ባህር ዳር፤ መጋቢት 30/2014(ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የምስረታ ዕድሜውን በሚመጥን መልኩ በአፍሪካ አስተማማኝና ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ሆኖ እንዲወጣ እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታወቁ።

የተቋሙን 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ሙሉ ዓለም ባህል ማዕከል  ተከፍቷል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሰይፈ ደርቤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢዜአ ከምስረታው ጀምሮ በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ዜናና ዜና ነክ ዘገባዎችን ለህዝብ በማቅረብ  ውጤታማ  ስራዎች ሲያከናውን ቆይቷል።

ተቋሙ 80ኛ ዓመቱን የሚያከብረው ያለፈውን ታሪክ  ብቻ ለመዘከር ሳይሆን ጠንካራ ሥራዎቹን በማስቀጠልና ድክመቶቹን በማረም የሀገርና የህዝብን ሰላም፣ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ በሚካሄደው እንቅስቃሴ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ቁርጠኛ  መሆኑን ለማሳየት ነው።

"ሀገሪቱ ውስብስብ ችግሮች ቢገጥማትም ኢዜአ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በግንባር ቀደምትነት ሚዛናዊ ዘገባዎችን ለህዝብ እያደረሰ ይገኛል" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤  በዓሉ ተቋሙን ወደ ፊት  ለማምጣት መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የምስረታ ዕድሜውን በሚመጥን መልኩ  በአፍሪካ አስተማማኝና ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ሆኖ ለመውጣት  የሚያስችለውን ዘመናዊ የቴሌቪዥንና የራዲዮ ስቱዲዮዎች ያሉት የሚዲያ ኮምፕሌክስ ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑንም አቶ ሰይፈ አስታውቀዋል።

ይህም ክልላዊ፣ ሀገራዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የዘገባ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው፤ ኢዜአ በክልሉ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ያለ ፣ አንጋፋና ተቀራርቦ በመስራት ረገድ ጥሩ ልምድ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ላይ ሚዛናዊ ዘገባዎችን ሰርቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙሃን  በመስጠት አሻራውን ያስቀመጠ ተቋም መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

"ባሳለፍናቸው ጥቂት የቀውስ ዓመታት ሚዛናዊ ዘገባ በመስራትና ነጻ ሚዲያ ሆኖ በመንቀሳቀስ ችግሮችን በማርገብ ሀገራዊ ለውጡ ወደፊት እንዲራመድ ትልቅ ሥራ እየሰራ ያለ ሚዲያ ነው" ብለዋል።

ኢዜአ አንጋፋነቱን ተጠቅሞ ስራውን  እንዲያጠናክርና ለሌሎችም አስተማሪ ሆኖ እንዲቀጥል የክልሉ መንግስት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ግዛቸው አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ህብረተሰቡ በቂ መረጃ ኖሮት ምክንያታዊነትን እንዲያጎለብት እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።

በከተማዋ የሚካሄዱ የልማት፣ የፖለቲካና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ተከታትሎ በመዘገብና የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በሙያ በመደገፍ  የጎላ አስተዋጾ ማድረጉን ጠቅሰዋል።  

"ተቋሙ እስካሁን የተጓዘበት መንገድ የሚበረታታ ነው" ያሉት ዶክተር ድረስ፤ በቀጣይ ለበለጠ ውጤት እንዲበቃ በሚያስፈልገው ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደማይለየው አረጋግጠዋል።

ለሶስት ቀናት ክፍት ሆኖ በሚቆየው አውደ ርዕዩ የመክፈቻ ስነ-ሥርዓት ላይ የክልሉና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን  በርካታ ህዝብ ይጎበኘዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ቀደም ሲልም ተቋሙ የተመሰረተበት  80ኛ ዓመት  በዓል  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በፓናል ውይይትና አውደ ርዕይ ፤ ቀጥሎም በተመሳሳይ መረሃ ግብር  በአዳማ ከተማ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም