ማዕቀብ ሰብዓዊ ቀውስን ያባብሳል፤ ችግር ያጋጠማቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ይጎዳቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ማዕቀብ ሰብዓዊ ቀውስን ያባብሳል፤ ችግር ያጋጠማቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ይጎዳቸዋል
መጋቢት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ማዕቀብ የሰብዓዊ ቀውስን ያባብሳል፤ ችግር ያጋጠማቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ይጎዳል ሲል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ተናገረ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለማሳለጥ ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን በአዎንታ እንደሚመለከተው ተቋሙ ገልጿል።
የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልዑክ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ፋቲማ ሳቶር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የሰሜኑ ጦርነት ከተከሰተ ጀምሮ ድጋፍ እያደረገ ነው።
በዚህም በትግራይ፣ በአማራና በአፋር በችግር ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን የህክምና፣ የምግብና የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ጎን ለጎንም በቅርቡ መንግሥት ያደረገው ግጭት የማቆም ውሳኔ ተቋሙ በአዎንታዊ እንደሚመለከተው ገልጸው ይህም የሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ ይረዳል ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የቀይ ማስቀል ኮሚቴ ባለፉት ሁለት ወራት በየቀኑ በሚባል ደረጃ 40 የሕክምና ድጋፍ የያዙ በረራዎች ወደ ትግራይ ክልል ማድጉንም ተናግረዋል።
ተቋሙ በሶማሌ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ለሚገኙ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ከብቶች የክትባትና የመኖ ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።
በተለይም ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመሆን ድጋፉን ለማሳለጥ እየሰራን ነው ብለዋል።
ተቋሙ በችግር ላይ ለወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች የህክምና ቁሳቁስ፣ የምግብና የውሃ መሳቢያ መሳሪያዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ይህንንም የድጋፍ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።እንደ ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋም ማዕቀብ ያሳስበናል፤ ምክንያቱም ማዕቀብ የሰብዓዊ ቀውሱን ያባብሰዋል፤ ጉዳት በደረሰባቸው አገራት የሚኖሩ ሰዎችን ይጎዳል።
ድርጅታቸው በማዕቀብም ጭምር የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የመደገፍ ሃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።