አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትብብር በማረም መቀጠል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትብብር በማረም መቀጠል ይገባል
መጋቢት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ የህዝብን ፍላጎት እንዲመልስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትርፍ ሳያሰሉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትብብር በማረም መቀጠል ይገባል።
ኢዜአ የሀገራዊ ምክክሩን በተመለከተ ከአዋጅ ማውጣት ጀምሮ እስከ ኮሚሽነሮች ምርጫ በነበረው ሂደት ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ፀሐፊና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ባፌ በወቅቱ እንዳሉት፤ መንግስት የብሔራዊ መግባባት ጉዳይን በባለቤትነት ይዞ የሀገራዊ ምክክር አዋጅ እንዲወጣና ኮሚሽኑ እንዲመሰረት ማድረጉ በጎ እርምጃ ነው።
ሆኖም የኮሚሽኑ የማቋቋም ሂደትና የኮሚሽነሮች ሹመት ከጅምሩ አካታች ያልነበረ፣ የማቋቋሚያ አዋጁን ድንጋጌዎች ያላከበረ እንደሆነ በመግለጽ ሞግተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአንዴም በላይ ሁለትና ሶስት ጊዜ መገናኘት የቻሉበት ዕድል ቢፈጠርም የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርሻ እንዳልነበራቸውና የሃሳብ ልዩነታቸው እንዳልተከበረ ጠቅሰዋል።
“የፖለቲካ ፓርቲዎች ለውይይት ቢጋበዙም የሀሳብ ልዩነታቸውን ያላስተናገደ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ፀሐፊና የኮሚሽነሮች የጥቆማ ተቀባይና አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ሄኖክ ስዩም በበኩላቸው፤ በዶክተር ራሄል የተንጸባረቁት ሀሳቦች ተቀባይነት የሌላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል።
“ኮሚሽኑን የማቋቋምና ኮሚሽነሮችን የመሾም ሂደቱ አሳታፊ፣ ግልፅና ህግን የጠበቀ ነበር” በማለት አስረድተዋል።
በቀረቡት እጩ ኮሚሽነሮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተያየት መስጠት እንዲችሉ መደረጉንም ተናግረዋል።
የአዋጁ ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ የኮሚሽነር ጥቆማ፣ ጥቆማውን የማደራጀት፣ እጩዎችን የመመልመል፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ 11 ኮሚሽነሮችን የመሾም ሂደቱም በግልጽ መንገድ መከናወኑን አብራርተዋል።
በተለይም የኮሚሽነሮች ጥቆማ በአዋጁ ላይ በተቀመጠው መስፈርትና መርሆ መሰረት ለህዝብ በይፋ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ቀርቦ ጥቆማው በአካልና በተለያዩ የዲጂታል መሳሪያዎች መከናወኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም 8 ሺህ ጠቋሚዎች 632 ግለሰቦችን የጠቆሙ ሲሆን፤ መስፈርቱን ያሟሉ 42 ግለሰቦች በእጩነት መቅረባቸውን ተናግረዋል።
የ8 ሺህ ጠቋሚዎችንና የ632 ተጠቋሚዎችን ዝርዝር መረጃ እጩዎች የተጠቆሙበትን መስፈርት በሰነድ ተዘጋጅቶ ስለሚገኝ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መመልከት ይችላል ነው ያሉት።
የ42ቱ ግለሰቦች አጠቃላይ የስራና የህይወት ዳራ ለህዝብ ይፋ መሆኑን በማንሳት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሀሳብ የሰጡ ሲሆን ያቀረቧቸው ሀሳቦችም እንዲካተተቱ ተደርጓል ብለዋል።
ዶክተር ራሄል ከ42ቱ እጩዎች መካከል የኢህአዴግ አባል የነበሩና መንግስትን ሲያማክሩ የነበሩ ግለሰቦች በኮሚሽነርነት መሾማቸውን በመጥቀስ ሂደቱ ላይ ችግር እንዳለ ተከራክረዋል።
"በኢህአዴግ ዘመነ ስልጣን ሀላፊነት ላይ የነበሩ ግለሰቦች በኮሚሽኑ መካተታቸው ከአዋጁ የሚቃረን ጉዳይ ነው" በማለትም የአዋጁ መርሆ አልተከበረም የሚል አቋም ይዘዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ ለኮሚሽነርነት ካስቀመጣቸው መስፈርቶች "የመንግሥት ሠራተኛ ያልሆነ የሚል መሥፈርት የለውም" የሚሉት ዶክተር ሄኖክ፤ አዋጁ ያስቀመጠው የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ የሚለው መርሆ መከበሩን ገልጸዋል።
በሂደቱም የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ለኮሚሽነርነት እጩ የሆኑ ግለሰቦች ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ ተደርጎ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆነ ሰው አለመኖሩን አረጋግጠዋል ነው ያሉት።
መስፈርቶቹን በመሻር የተሾመ ኮሚሽነር የለም ያሉት ዶክተር ሄኖክ፤ ማስረጃ አለኝ የሚል ካለ ማምጣትና ቅሬታ ማቅረብ እንደሚችል ጠቅሰዋል።
ዶክተር ራሄል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን አዋጅ እና መሰረተ ሀሳቡን እንደሚቀበሉ አዋጁም መተግበር እንዳለበት ጠቅሰው፤ መንግስት አስተያየቶችን ለመቀበል በሩን መክፈት አለበት ብለዋል።
በቀጣይም ሀገራዊ ምክክሩ ሂደት መሳካት ፖለቲካዊ ፈቃደኝነቱን እንዲያረጋግጥና ሚናውንም በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የሴራና የመጠላለፍ ፖለቲካ ሀገርን መጉዳቱን ያነሱት ዶክተር ሄኖክ ሀገሪቱን ለረጅም ዓመታት እረፍት ከነሳት ኋላቀር የፖለቲካ ጉዞ መውጣት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉ ሲሆን በማንኛውም ጉዳይ ላይ ምክክርና ውይይት ተደርጎ ወደ መግባባት እንደሚደረስ ተስፋቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥና ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የምክክሩ ዋና ባለቤት የሆኑ ኢትዮጵያውያንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ