ቀጥታ፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች ያወጡት ሪፖርት በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃገብነት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ኢትዮጵያ አትቀበለውም

መጋቢት 30 ቀን 2014- (ኢዜአ)  አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች ከሰሞኑ ያወጡት የጋራ ሪፖርት ፖለቲካዊ ፍላጎትና ጣልቃገብነት የተንጸባረቀበት በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትናንት ማምሻውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከኮቪድ-19 ወረረሽኝ በኋላም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በለኮሰው ጦርነት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅና በሌሎች ውጫዊ ጫናዎች ፈርጀ-ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል።

ይሁንና መንግሥት የአገሪቷን ሉዓላዊነትና የሕዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሸባሪው ቡድን ግን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ሲያውክ እንደነበር ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ድጋፍ የዜጎች ሕልውና ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት መሥራቱን አንስተዋል።

በሌላ በኩል አገሪቷ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የብሔራዊ ምክክር መድረክ ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት በኩል የሚቀርቡ የሰላም አማራጮችን እየጠበቅን ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በቅርቡ መንግሥት የወሰነው የሰብዓዊ ግጭት ማቆም ውሳኔም መንግሥት ላልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስና ሰላም እንዲረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከሁሉም አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና የውስጥ ሰላም ለማረጋገጥ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ ያም ሆኖ በአንዳንድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኩል የኢትዮጵያን ጥረት ያለማክበርና ዕውቅና የመንሳት አዝማሚያዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ጦርነቱ በተካሄደበት ሥፍራዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አጣርቶ የወንጀል ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም ቀደም ብሎ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ በተካሄደው ምርመራ መሰረት በሁሉም ወገን ያሉ የመብት ጥሰት የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ኮሚቴ አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በቅርቡ የአምነስቲ ኢንተርናሽናልና በሂዩማን ራይት ዎች በተሰኘው ሰብዓዊ መብት ተቋም የወጣው  ሪፖርት ግን የአንድ ወገን የፖለቲካ ፍላጎት የተንጸባረቀበት በመሆኑ በመንግሥት ተቀባይነት የሌለው ሪፖርት እንደሆነ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ ተቋም እንደሆነ ገልጸው፤ ኮሚሽኑ ለሚያወጣቸው ተጨባጭ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችን ታማኝነት የሌላቸው በማስመሰል የሚገልጹ ዓለም አቀፍ ተቋማትንም ኮንነዋል።

በሌላ በኩል በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈጸሙ ጥፋቶች ጥምር ምርመራ እንዲደረግ መንግሥት በሩ ክፍት መሆኑንም ነው ያረጋገጡት።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላት ላይ የወንጀል ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በምርመራ ሂደቶች ላይ ብዙ ርቀት እንደሄደች ገልጸዋል።

የወንጀል ምርመራ ሥራው ግጭት በነበረባቸውና ወንጀል ተፈጽሟል ተብሎ የሚታመንባቸው አካባቢዎችን ሁሉ ያካተተ እንደሆነና ቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ የመጨረሻውን ውጤት ሲጠናቀቅም ክስ ይመሰረታል ብለዋል።

በተለይም የጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎችን ሥነ-ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፍ ለመስጠት የተለያዩ የኃብት ማሰባሰብ ሥራዎች መከናወናቸውንና መንግሥት ተጨማሪ በጀት እንዲመድብ የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ-ኃይል መወሰኑን አንስተዋል።

እስካሁን የምርመራና ክስ ኮሚቴው ከ10 ሺህ በላይ የምስክሮችን ቃል ማሰባሰቡን ገልጸው፤ በምርመራው ጥፋተኛ የሆነ አካል ማንም ይሁን ከማን ወገን ተጠያቂ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህን የአገር ውስጥ ሰብዓዊ መብትና የፍትህ ተቋማት የሚያደርጉትን የወንጀል ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሂደት ከማደናቀፍ ይልቅ እውቅና መስጠትና ማገዝ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም