ቀጥታ፡

ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የሰላም መንገድ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

አዲስ አበባ ነሃሴ 30/2010 ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የሰላም መንገድ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በኤርትራ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ የኤርትራን ወደብ መጠቀም አቁመው የነበሩ የኢትዮጵያ መርከቦች ከ20 አመታት በኋላ  ስራ ለማስጀመር 'መቀሌ' የተሰኘችው መርከብ በምጽዋ ወደብ መልህቋን ስትጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ተገኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የተጀመረው የሰላምና የመግባባት ሂደት ውጤት እያሳየ ነው። የመርከቧን ከ20 አመታት በኋላ ስራ መጀመር የሰላም ማስፈን ተጨባጭ ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል። ''ምጽዋ ላይ በተጨባጭ ስራ መጀመሩንና የአሰብ ወደብም የሚያስፈልገውን ዝግጅት እየጨረሰ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መንገዶቹ ለወደብ እቃ ማመላለሻና ሌሎች ጉዳይ ማገልገል የሚችሉ ናቸው'' ብለዋል። ትንሽ ችግር ያለበት ዛላንበሳ አካባቢ አስፈላጊው ጥገና ሊደረግለት መሆኑንም ጠቁመዋል። የሰላምና የትብብር ሂደት ፍጥነቱ ለአለም ሁሉ ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ''አዲሱን አመት በአዲስ ተስፋ እንቀበላለን ላልነውም ትልቅ ተስፋ ነው'' ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቻይና አፍሪካ ጉባዔን አጠናቀው ዛሬ ማለዳ ኤርትራ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አሰብ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል። በምጽዋ ወደብ መቀሌ የሚል ስያሜ ያላት የኢትዮጵያ መርከብ ዛሬ 11 ሺህ ሜትሪክ ቶን የወጪ ንግድ ምርቶች ይዛ ወደ ቻይና ታመራለች። መርከቧ ወደ ቻይና የምታደርገው ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስም የተሰየመ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወደቡ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን አበረታትተዋል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባትና ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ስትጠቀም የቆየች ሲሆን በቅርቡ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ የኤርትራ ወደቦችን ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ተደርሷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም