ቀጥታ፡

ኢዜአ ሚዛናዊ ዘገባዎችን በመስራት በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን በማርገብ አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው- ቢሮው

ባህር ዳር፣  መጋቢት 30 ቀን 2014- (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ታሪክ ፋና ወጊ የሆነው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሚዛናዊ ዘገባዎችን በመስራት በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን በማርገብ አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው" ሲል የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በባህር ዳር ከተማ ለሦስት ቀን ያዘጋጀውና የድርጅቱን የዓመታት ጉዞ የሚያሳየው አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፍቷል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅቱ እንደገለጹት "ኢዜአ ሚዛናዊ ዘገባዎችን በመስራት በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን በማርገብ አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው" ብለዋል።

በተለይም በክልሉ በነበረው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ወቅት ችግሮች እንዳይባባሱ በማድረግ የላቀ ሚና መጫወቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"ኢዜአ እያበረከተ እንዳለው አስተዋፅኦ ተገቢውን ድጋፍ አላገኘም" ያሉት አቶ ግዛቸው፣ በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

አውደ ርዕዩን በክብር እንግድነት ተገኝተው የከፈቱትና የጎበኙት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ እንዳሉት፣ ድርጅቱ በአገሪቱ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ግንባታ ግንባር ቀደሚ ሚና ተጫውቷል።

ባህር ዳር ከተማን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚካሄዱ የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎችን በመዘገብ የህዝብ ወገንተኝነቱን ያረጋገጠ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ድርጅቱ የሚያጋጥመውን ተግዳሮት በመፍታት የሥራ አፈፃፀሙን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚያደርገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፣ ኢዜአ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከ36 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት አንጋፋ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።

ድርጅቱ ባሉት ቅርንጫፎች በመላ አገሪቱ ተደራሽነቱን በማስፋት የህዝብ ድምፅ እንዲሆን ያስቻለው መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት 80ኛ ዓመቱን ሲያከብር አራት የሬድዮና ሦስት የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎችን የያዘ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አስገንብቶ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ተቋሙ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ያለውን ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድገው ያላቸውን እምነት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሰይፈ  ደርቤ አስታውቀዋል።

ዛሬ በባህር ዳር ሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል ለህዝብ ክፍት በሆነው አውድ ርዕይ የኢዜአን የ80 ዓመታት ጉዞ የሚያስቃኙ የቪዲዮና የፎቶግራፍ መረጃዎች ለእይታ ቀርበዋል።

አውደ ርዕዩም ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም