ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የተሰረቁ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የመሠረተ ልማት ቁሶች ከተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ድሬዳዋ ፤ መጋቢት 30/2014 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር የተሰረቁ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመሠረተ-ልማት ቁሶች በድርጊቱ ከተጠረጠሩ ግለሰቦች ጋር በቁጥጥር ሥር በማዋል ክስ መመስረቱን ፖሊስ አስታወቀ።

የድሬዳዋ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ታክቲክ ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር መሐመድ ኢብራሂም ለኢዜአ  እንዳሉት ፤ በከተማው የመሠረተ-ልማት አውታሮች ላይ እየተፈፀመ የሚገኘው ስርቆት እየጨመረ  መጥቷል፡፡

ስርቆት ከሚፈጸምባቸው መካከል የኢትዮ-ቴሌኮም የፋይበር ኦፕቲክ መስመሮች ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ገመዶች፣ የውሃ ቱቦዎችና የምድር ባቡር ሃዲዶች ይገኙበታል፡፡

የሚፈጸመውን ዘረፋ ከምንጩ ለማድረቅ ከወትሮ በተለይ መንገድ የምርመራ ቡድን በማዋቀር የተዘረፉ ሀብቶችን በተደበቁበት ስፍራ ከየካቲት 4/2014ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በተደረገ ብርበራ  1 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ንብረቶችንና በድርጊቱ የተጠርጠሩ ግለሰቦችን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

በስርቆቱ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦችና የተሰረቁ ንብረቶቹን የሚቀበሉ ሁለት  የኮንስትራክሽን መሳሪያ ሽያጭ ነጋዴዎች ተይዘው ጉዳያቸው ተጣርቶ በአቃቤ ህግ ክስ  እንደመሰረተባቸው  አስታውቀዋል፡፡

ኮማንደር መሐመድ "ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የሚመጡ የመንግስትና የህዝብ መገልገያ ሃብቶችን እንደ  ተራ ብረት አንዱን ኪሎ በ3 መቶ ብር ሲሸጡ ነበር"  ብለዋል፡፡

"አሰሳውና ተጠርጣሪ አካላትን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ  ቀጥሏል " ያሉት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን  ለመከላከል በሚደረገው ሂደት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በቴሌኮም መሠረተ-ልማት ላይ የሚካሄደው ስርቆትና ዘረፋ እንደ ሀገር ያለ ችግር መሆኑን የገለጹት የምስራቅ ሪጅን ኢትዮ-ቴልኮም የጥገናና የመደበኛ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት መስፍን ናቸው።

ወንጀሉን በሚፈጽሙት ላይ አስተማሪና ተመጣጣኝ  ህጋዊ ቅጣት መውሰድ እንዳለበትም አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ የራሱን መገልገያ መሰረተ-ልማቶች ከስርቆት ማዳን እንዲችል ከፖሊስ ጋር በመሆን የግንዛቤ ማሳደግ ሥራን እንደሚሰራ  ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ ለመሠረተ-ልማቶች የሚያደርገውን ልዩ ጥበቃና ክትትል ህብረተሰቡ እንዲያግዝ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ትዕግስት ተሾመ ናቸው፡፡

በዚህም ህብረተሰቡ በቴሌኮምና በመብራት ኃይል መሠረተ-ልማቶችን ጨምሮ በሌሎችም የህዝብ አገልግሎት መስጫዎች ላይ  የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎችን በመከላከል ተግባር የድርሻውን  መወጣት ጀምሯል ብለዋል፡፡

መሰል ወንጀሎችን የመከላከል ተግባር ያለ ህብረተሰቡ  የነቃ ተሳትፎ መከላከል አዳጋች በመሆኑ ድጋፉን ለማጠናከር የንቃተ ህግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም