ቀጥታ፡

ከፈተናዎቿ የገዘፈች አገር

ከፈተናዎቿ የገዘፈች አገር

ከፈተናዎቿ የገዘፈች አገር

የአራት ዓመታት ውጣ ውረዶች እንደማሳያ

  • የሃሳብ ልዩነትን ለማፈን የወጡ ህጎችና አዋጆች በፍጥነት መሻሻላቸው፣ መንግስትን በመቃወማቸው ብቻ የታሰሩ አካላት ከእስር መፈታታቸው ትልቅ ስኬት ነው፡፡
  • ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሃብት ከማፍራት አኳያ ዛሬም አያሌ ፈተናዎች አሉ፤ ዜጎች ይፈናቀላሉ፣ የታጠቁ ቡድኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ፡፡
  • በግብርናው መስክ ከተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች ውስጥ የቆላ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡
  • የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ዛሬም እንደከበደ ነው፤ የኑሮ ውድነት ኢትዮጵያዊያንን በእጅጉ እየፈተነ ነው፡፡

5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እለተ ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው የ3ኛ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ዶክተር ዐቢይ አህመድን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሰየሙ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሹመቱን ተከትሎ በምክር ቤቱ አባላት ፊት 35 ደቂቃ ከ 31 ሰከንድ የወሰደ ንግግር አድርገዋል፡፡

ዶክተር ዐቢይ አህመድ  የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ በኋላ፤ ለመላው የሀገራችን ህዝብ ካሰሙት ንግግር ውስጥ ስለ ስልጣን ሽግግሩ የገለፁት እውነታ አይረሳም። እርሳቸው እንዳሉት የስልጣን ሽግግሩ ሁለት አበይት እውነታዎችን የሚያመላክት ነው።

የሽግግሩ ክስተት በአንድ በኩል በሀገራችን ዘላቂ፣ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ ህገ መንግስታዊ ስርዓት መሰረት ለመጣላችን ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው በሌላ በኩል ደግሞ፤ ከጊዜው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝ እንዲሁም በህዝብ ፍላጎት ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ስርዓት እየገነባን መሆኑን ያመላክታል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በአጠቃላይ ንግግራቸውም ኢትዮጵያዊያን ያለፉበትን ታሪክና የወደፊት መጻኢ እድል ያስቃኙ ሲሆን፤ መንግስታቸው  ስለሚያከናውናቸው ተግባራትም ይፋ አድርገዋል፡፡ ንግግራቸውም በዋናነት የመንግስታቸውን የቀጣይ ኢኮኖሚዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና የመልካም አስተዳደር መንገዶች አቅጣጫ ያሳየ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ካነሷቸው ሃሳቦች የትኞቹ ተሳኩ? የትኞቹስ ፈተና ገጠማቸው?

ፓለቲካ

“የኔ ብቻ ሃሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ የሚል አካሄድ አገር ያፈርሳል፤ የሃሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በዳሰሱበት ንግግራቸው የሃሳብ ልዩነት እንዲከበር አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ዴሞክራሲና የሃሳብ ነጻነት የማይነጣጠሉ ጉዳዮች በመሆናቸው፤ ከዚህ አኳያ “ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም መንግስትን በመቃወማቸው ብቻ የታሰሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ከእስር የተፈቱ ሲሆን በውጭ አገር ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ፖለቲከኞችና ነፍጥ አንስተው  በረሃ የወረዱ ኃይሎች ወደ አገራቸው በሰላም እንዲገቡ ተደርጓል።

የሃሳብ ልዩነትን ለማፈን የወጡ ህጎችና አዋጆች በፍጥነት እንዲሻሻሉ የተደረጉ ሲሆን በዚህ ረገድ የጸረ-ሽብር ህጉና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ይጠቀሳሉ፡፡ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲደመጡና ልዩነቶች ወደ ጠረጴዛ እንደሚመጡ የሚያስችሉ ነጻ የውይይት መድረኮችም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተነሳሽነት ጭምር እንዲካሄዱ ተደርገዋል፡፡

በዚህ ረገድ “የአዲስ ወግ” የውይይት መድረክ ለአብነት የሚነሳ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎችም ፖለቲከኞች የፈለጉትን ሃሳብ የሚያነሱበት የውይይት ባህል እንዲጎለብቱም ተደርጓል፡፡ መገናኛ ብዙሃን የፈለጉትን ሃሳብ የሚያራምዱበት ስርዓት በመፍጠር በአሸባሪነት የተፈረጁ የመገናኛ ብዙሃን ወደ አገር ቤት በመግባት የሃሳብ ነጻነትን እንዲያጣጥሙ መደረጉም የሃሳብ ልዩነትን በማክበር በኩል የተሳካ ተግባር ስለመከናወኑ አመላካች ነው፡፡

“ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጸር እንደተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፤ እንደጠላት ሳይሆን እንደወንድምና አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው”  ባሉት መሰረት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ለህዝቡ አማራጭ ሃሳብ አቅራቢ ስለመሆናቸው በንግግራቸው ማብራራታቸው አይዘነጋም፡፡

ይህንን ተከትሎም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ፓርቲዎች በአገር ጉዳይ በጋራ የሚሰሩበትን መንገድ በመክፈት ከኢህአዴግ ወደ ውህድ ፓርቲ የተቀየረው ብልጽግና ፓርቲ 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ አሸንፎ አገር ለመምራት ካቤኔዎችን ሲያዋቅር የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አካቷል፡፡

ይህ አዲስ የፖለቲካ ባህል በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሳይታጠር ክልሎችም በተመሳሳይ በካቢኔዎቻቸው የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማካተት አዋቅረው ህዝብን በጋራ እየመሩ ነው፡፡

“ተቃዋሚ” የሚለው አሉታዊ ቃልም ተቀይሮ  ቀላል በሚመስል ግን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ግብር በሚገልጽ “ተፎካካሪ” በተሰኘ ቃል ተተክቷል፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገዢና ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ያለው መስተጋብር ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ተግባራትን አከናውነዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የህግ የበላይነት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ “ህዝባችን የሚፈልገው የህግ መኖርን ብቻ ሳይሆን ፍትህ መረጋገጥን ጭምር ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ንግግራቸው በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሃብት የማፍራት መብታቸው እንዲከበር መንግስታቸው እንደሚሰራ መጠቆማቸው አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት በመጡ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የተሻለ ስራ ቢያከናውኑም፤ ኢትዮጵያ ካለችበት ስር የሰደደ ችግር ማላቀቅ አልቻሉም፡፡

ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሃብት የማፍራቱ ጉዳይ አሁንም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ አሁንም ዜጎች ይፈናቀላሉ፤ የታጠቁ ቡድኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ፡፡ የህግ የበላይነትን ማስፈንና ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሃብት የማፍራት መብታቸውን ማስከበር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መንግስታቸው ቀጣይ የቤት ስራ መሆኑ እሙን ነው!

ኢኮኖሚ

“በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም ዘርፉን በሚገባው ደረጃ በቴክኖሎጂ መደገፍ ባለመቻሉ የሚገባንን የኢኮኖሚ ትሩፋት ሳናገኝ ቀርተናል”

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚውን መስክ በዳሰሰው ንግግራቸው የዋጋ ንረትን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን፣ የእዳ ጫናንና ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋትን በሚመለከት ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርናውን ክፍለ-ኢኮኖሚ ማዘመን በሚቻልበት ሁኔታም ሰፋ ያለ ማብራሪያ መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኃላፊነት ዘመናቸው እጅጉን የተሳካ ስራ ካከናወኑባቸው መስኮች አንዱ ግብርናው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በወቅቱ ግብርናውን ማዘመን የሚችሉ እንደ ትራክተር ያሉ ግብዓቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአርሶ አደሩ እንዲከፋፈሉ ማድረግ ከመቻላቸው በላይ በርካታ የአነስተኛ ግድቦች ግንባታም በፍጥነት እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያ በጦርነት፣ ድርቅ እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ውስጥም ሆና ጉልህ ተጽእኖ ሳይደርስባት ችግሮችን መቋቋም የቻለችው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርናው መስክ ካከናወኗቸው ውጤታማ ስራዎች ውስጥ የቆላ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡ ወደ ስልጣን በመጡ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ረሷን ለመቻል እንድትንደረደር አድርገዋታል፡፡

ለአብነትም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በበጋ መስኖ ለማምረት የተጀመረው ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርናው መስክ ለማከናወን የገቡትን ቃል በትክክል እየተገበሩ ለመሆኑ አመላካች ነው፡፡

በኢኮኖሚው መስክ ያነሱት ሌላኛው ሃሳብ የወጪ ንግድን በማስፋት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን መቅረፍ ሲሆን በዚህ በኩል በ2013 በጀት ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ወጪ ንግድ ብቻ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡ ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማጎልበት የተከናወኑ ተግባራትም ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቅረፍ የተከናወነው ተግባርም በስኬት የሚነሳ ነው፡፡ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ የስንዴ ምርትን በአገር ውስጥ ለመተካት የተሄደበት ርቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቅረፍ የሰጡትን ትኩረት አመላከች ነው፡፡

ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆን የድንጋይ ከሰልን በአጭር ጊዜ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል ውጤታማ ተግባር ተከናውኗል፡፡ ምናልባትም ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ኢትዮጵያ የድጋይ ከሰል ፍላጎቷን ሙሉ ለሙሉ በራሷ አቅም የምትሸፍን ይሆናል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛረን በማስቀረት ረገድ ያለው ሚና ጉልህ ነው፡፡

ጤናማ የፋይናንስ ስርዓትን በመፍጠር ረገድም የብር ኖትን እስከመቀየር የደረሰ እርምጃ ወስደዋል፡፡ በዚህም በፋይናንስ አሻጥር ውስጥ ተሰማርተው ዘርፉን ሲበዘብዙ የነበሩ ቡድኖችን ፍላጎት ማምከን ተችሏል፡፡ በብር ኖት ቅያሪው ምክንያት በርካታ ሃብት በህጋዊ የፋይናንስ ዝውውር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ስርዓቱን ለማሻሸል የሄዱበትን ርቀት የሚያሳይ ሲሆን፤ በሂደቱም አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረውን የህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀልን መቀነስ ተችሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን በሚያደርጉበት ወቅት ኢትዮጵያ በእዳ ጫና ምክንያት ከየትኛውም አገር ሆነ ተቋም መበደር ወደ ማትችልበት ደረጃ ተሸጋግራ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የእዳ ጫና ለማቃለል እንደሚሰሩ በሰጡት ማረጋገጫ መሰረትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ተለያዩ አገራት በመጓዝ የኢትዮጵያን እዳ ማሰረዝ ችለዋል፡፡ በ2011 በጀት ዓመትም መከፈል የነበረበትን እዳ በመክፈል የኢትዮጵያን የእዳ ጫና ማቃለል ችለዋል፡፡

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ባስቀመጡት ልክ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት አልቻሉም፡፡ የዋጋ ንረት አሁንም ኢትዮጵያዊያንን በእጅጉ እየፈተነ ነው፡፡ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደረው የህብረተሰብ ክፍል በልቶ ማደር እጅግ አዳጋች እየሆነበት መጥቷል፡፡

በእርግጥ ባለፉት ሶስት ዓመታት ዳቦ በዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎችን እንዲገነቡ ከማድረግ ባሻገር ግዙፍ የዘይት ፋብሪካዎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ አምጥተዋል ብሎ ደፍሮ ለመናገር ግን አዳጋች ነው፡፡

ዲፕሎማሲ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ዲፕሎማሲን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀጣናው ካሉ አገራት ጋር ስለሚኖራት መተሳሰር ያነሱ ሲሆን፤ በተለይ ኤርትራን በሚመለከት ያደረጉት ንግግር እጅግ ድንቅ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ “ከኤርትራ መንግስት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የነበረው አለመግባባት እንዲያበቃ ከልብ እንፈልጋለን፤ በደም ለተሳሰሩ የሁለቱ አገር ህዝቦች ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪየን አቀርባለሁ”  ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም ወደ አስመራ በማቅናት ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኤሳያስ አፈወርቂ ጋር ተነጋግረው ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የቆመውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ ችለዋል፡፡ በዚህ አኩሪ ተግባራቸውም የዓለም የሰላም ሎሬት ለመሆን በቅተዋል፡፡

በቀጣይ ወደ ሁሉም የቀጠናው አገራት በማምራትም ቀጠናዊ ትብብርን ለማጠናከር  ሰርተዋል፡፡ የሱዳን ኃይሎች ችግሮቻቸውን በሰላም እንዲፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም የዓለም አቅጣጫ የሚኖራትን የዲፕሎማሲ ተጽእኖ ከፍ ለማድረግ ወደ በርካታ አገራት ተጉዘው ከፍተኛ ስራ አከናውነዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዲፕሎማሲው መስክ ቃላቸውን በተግባር በመፈጸም ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

መልካም አስተዳደር

“የህዝባችንን ብሶት ካባባሱ ጉዳዮች አንዱ ሙስና ነው፤ ኢትዮጵያ አንዱ ለፍቶ ሌላው ደግሞ ቀምቶ የሚኖርባት አገር መሆን የለባትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልካም አስተዳደርን ከዳሰሱበት ንግግራቸው ትኩረት የሰጡት የሙስናን ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህም መንግስታቸው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ሌብነትን ለመታገል እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ጉምቱ ባለስልጣናትን ከማሰር ጀምሮ ተቋማት ዲጂታል አሰራርን በመዘርጋት ለሙስና የማይመች ሁኔታን እንዲፈጥሩ ለማድረግ ጥረዋል፡፡ “ሙስና” የሚለውን ቃል በመተውም “ሌብነት” ተብሎ እንዲጠራ አርአያ በመሆን ሰርተዋል፡፡

ነገር ግን ሌብነትን በመቀነስ ረገድ በሚፈለገው ልክ ለውጥ አምጥተዋል ለማለት የሚከብድ ሲሆን አሁንም ሌብነት ህዝብን ያማረረ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏለ፡፡ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ከሰሞኑን በተለያዩ አከባቢዎች በመገኘት ባካሄዱት የህዝብ የውይይት መድረክም ህዝብ በሌብነት ጉዳይ እጅግ እንደተማረረ በተግባር ታይቷል፡፡

የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት

“ያለ ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አገር የትም ልትደርስ እንደማትችል እንረዳለን፤ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የተንዛዙ አሰራሮችን በማስወገድ መንግስት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” በማለት ወጣቶችን በሚመለከት ባደረጉት ንግግር “ወጣቶች ኢትዮጵያ የእናንተ ናት” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ መንግስታቸው በተለይ ለወጣቶች ተጠቃሚነት እንደሚሰራም ነበር ቃል የገቡት፡፡

ይህን ተከትሎም ወጣቶችን የሚመለከቱ በርካታ ተግባራትን ያከናወኑ ሲሆን በተለይ የወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት በተደራጀ መልኩ ለመምራት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲፈጠር ሆኗል፡፡

የስራ ፈጠራ ኮሚሽንም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት በተከናወኑ የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል ያገኙ ሲሆን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በርካታ ወጣቶች በችግኝ ማፍላት ተግባራት ተሰማርተው ስራ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ወጣቶች በቀላሉ ወደ ስራ እንዲገቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “easy of doing business” የተሰኘ ኢንሸቲቭ ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል፡፡ በዚህም ስራ ለመጀመር ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን መቅረፍ ችለዋል፤ አሰራሩ ወጣቶች ስራ ለመጀመር በቀላሉ ብድር እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ለሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን፤ “አገራዊ ማንነታችን ያለ ኢትዮጵያ ሴቶች ምንም ነው ግማሽ አካሉን የረሳ አገር ሙሉ የአገር ስእል ሊኖረው እንደማይችል መንግስት በውል ይገነዘባል’’ በማለት መንግስታቸው ለሴቶች እኩል ተሳታፊነት  እንደሚሰራ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ከካቢኔያቸው ግማሽ ያህሉን በሴቶች በማዋቀር ቃላቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዝዳንት እንዲሁም ሴት የመከላከያ ሚኒስትር እንዲኖራት በማድረግ ሴቶች እድሉን ካገኙ የተሻለ ተግባር ማከናወን እንደሚችሉ በተግባር እንዲያሳዩ እድል ፈጥረዋል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ ከመጋቢት እስከ መጋቢት ያለፉት አራት ዓመታት አያሌ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው መሆኑ እርግጥ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ አገርና ህዝብ ብዙ ፈተናዎችን የተጋፈጡባቸውም ነበሩ። በእርግጥ ኢትዮጵያዊያን ከፈተናዎቻቸው በላይ መሆናቸው በሚገባ ታይቷል። ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ የጥፋት በትሮች በሁሉም አቅጣጫ  ቢሰነዘሩም ካሳላፍናቸው ያለፍናቸው ይገዝፋሉ።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም