ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን የ80 ዓመት ጉዞ የሚያስቃኝ አውደ ርዕይ ነገ በባህር ዳር ይከፈታል

ባህር ዳር፤ መጋቢት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) የ80 ዓመት ጉዞ የሚያስቃኝ የቪዲዮና የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ነገ በባህር ዳር ከተማ እንደሚከፍት ተገለጸ።

አውደ ርዕዩ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የተቋሙ አመራሮች በተገኙበት እንደሚከፈት የኢዜአ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወንድይራድ ገልጸዋል።

በነገው ዕለት በሙሉ ዓለም ባህል ማዕከል ለህዝብ ክፍት የሚሆነው አውድ ርዕዩ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ መሆኑን ገልጸው፤ አውደ ርዕዩ የዝግጅቱ አካል መሆኑንም አመላክተዋል።

አውደ ርዕዩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ከአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ፣ ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን መምሪያና ከሌሎች አደረጃጀቶች ጋር በትብብር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በአውደ ርዕዩ ኢዜአ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የሰራቸውን ዜና እና ዜና ነክ ጉዳዮች፣ የመረጃ መቀበያና ማሰራጫ፣ የምስልና ድምጽ መቅረጫና ማስተላለፊያ የመሳሰሉት በየዘመኑ የተገለገለባቸው የስራ መሳሪያዎች ይቀርባሉ።በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት በነበረው የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ወቅት የኢዜአን ሚና የሚያሳዩ የቪዲዮ እና የፎቶ ግራፍ መረጃዎች የአውደ ርዕዩ አካል መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል የስራ ኃላፊዎች፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አውደ ርዕዩን እንደሚመለከቱት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) 80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ- በዓል በዋናው መስሪያ ቤት የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት በፓናል ውይይትና በአውደ ርዕይ መከበር ጀምሯል።

እንዲሁም በአዳማ ከተማ ከየካቲት 7 እስከ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ክፍት ሆኖ የቆየውን የቪዲዮና የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና በርካታ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ተመልክተውታል።

ኢዜአ በክልሎች በሚገኙ ቅርንጫፎቹ አማካኝነት በመላ ሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን ተከታትሎ ትክክለኛና ሚዛናዊ ዘገባዎችን አጠናቅሮ በማስላለፍ ሕዝብ በወቅቱ እንዲያውቃቸው እያደረገ ነው።

እንዲሁም በሀገር ገፅታ ግንባታ፣ በብሄራዊ መግባበትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ዘገባዎችን አጠናክሮ በማሰራጨት ሕዝቡ በሀገሩ ጉዳይ መረጃ ኖሮት ንቁ ታሳታፊ እንዲሆን እየተጋ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም