ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ረቂቅ ውሳኔው እንዳይጸድቅ የጀመሩትን ንቅናቄ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስገነዘበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ረቂቅ ውሳኔው እንዳይጸድቅ የጀመሩትን ንቅናቄ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስገነዘበ
ጎንደር መጋቢት 29/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች HR6600 ረቂቅ ውሳኔ እንዳይጸድቅ የጀመሩትን ንቅናቄ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስገነዘቡ ፡፡
አምባሳደሩ ሳምንታዊውን የውጪ ጉዳዮች ጋዜጣዊ መግለጫ በጎንደር ከተማ ዛሬ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው እንዳሉት በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ረቂቅ ውሳኔው እንዲዘገይ ተደርጓል፤ እንዲሁም ተሰርዟል የሚባለው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተረጋገጠ አይደለም፡፡
“የአሜሪካ ኮንግረስ ረቂቁን እንዲሰርዝ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ወዳጆቻችን ንቅናቄያቸውን ማስቀጠል አለባቸው” ያሉት አምባሳደሩ “ረቂቁ ለአሜሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግንኙነትና ለአካባቢው ሰላም ጠቀሜታ የለውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“መንግስት የአጎዋ ከቀረጥ ነጻ የገበያ እድል መሰረዙ ውሳኔው ትክክል አይደለም የሚል አቋም አለው” ያሉት አምባሳደሩ” ከአሜሪካን ጋር ትብብሩን እንፈልገዋለን፤ ግንኙነቱንም ለማሻሻል የበኩላችን ጥረት እንዳደርጋለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“በቅርቡ በጎንደር ዩንቨርሲቲ በተደረገ ጥናትና ምርምር የተገኘው የዜጎች የጅምላ መቃብር ተቋሙ ይህን ማድረጉ ለወገኑ መቆሙን የሚያሳይ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል” ብለዋል፡፡
“በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በጎንደር ዩንቨርሲቲ አማካኝነት የተገኘው የጅምላ መቃብር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ገለልተኛ የሆነ አካል ማጣራት ይችላል “ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነትን በተመለከተም በሀገራቱ መካከል ጥሩ ግንኙነትና መደጋገፍ እንደለ ጠቁመው “መደጋገፉ ይቀጥላል ብለን ተስፋ እንዳርጋለን” ብለዋል፡፡
“በቅርቡ በኤርትራ በኩል ለኢትዮጵያ የተሾሙት ኢትዮጵያን በደንብ የሚያውቁ በሳል ዲፕሎማት ናቸው” ያሉት አምባሳደር ዲና “ ከዚህ ተነስቶ ግንኙነቱ ዝቅ ብሏል፤ እየተቀየረ ነው፤ ወደ ሚለው ማጠቃለያ አንሄድም” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ 20 ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ የገቡ መሆኑን ጠቁመው መንግስት የሰብአዊ ድጋፉን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአሜሪካ እና አውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ ሁኔታ ላይ አዎንታዊና ገንቢ ውይይት ማካሄዳቸውን በመግለጫው አመልክተዋል።
የጂቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ዑመር ጌሌ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በተመከለተም ሁለቱ ሀገሮች በወደብ አጠቃቀምና በሌሎችም ኢኮሚያዊ ግንኙነቶች ላይ የጋራ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
“በጎንደር ዩንቨርሲቲ ዛሬ የተመሰረተው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማእከል የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያግዝ በመሆኑ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማእከሉ መጠናከር ማናቸውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው” ብለዋል፡፡
በሳምንታዊው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የሀገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙሀን ተሳትፈዋል፡፡