በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬም በፍቅር የጸናው የድሬዳዋ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ! - ኢዜአ አማርኛ
በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬም በፍቅር የጸናው የድሬዳዋ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት !
ሳምንቱ የድሬዳዋ የዘመናት ህብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆኑ እሴቶች የገነኑበትና ያበቡበት ነበር ማለት ይቻላል። ለውትሮም ቢሆን በፍቅር ከተማነቷ የማትታማው ድሬደዋ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና እምነት ተከታዮች ሕብረት ፈጥረው የሚኖሩባት ከተማ ናት። በእዚህም "ትንሿ ኢትዮጵያ" እየተባለች ስትጠራ ይደመጣል።
ጊዜው ለክርስትና እና ለእስልምና እምነት ተከታዮች የአብይ እና የረመዳን ጸም ወቅት መሆኑን ተከትሎ ህበረ ብሔራዊነቱ፣ አብሮነቱና መተሳሰቡ ይብልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ባለፈው ሣምንት የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የለገሃሬ ወጣቶች በድሬዳዋ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከፀሎት ስርአት ለተመለሱ ክርስቲያን እህትና ወንድሞቻቸው ምግብና መጠጦችን አዘጋጅተው ቀኑን በታላቅ ፍቅርና በአንድነት አሳልፈዋል።
በተመሳሳይ ወጣቶች ባስተባበሩት የረመዳን ፆም መግቢያ ምሽት ላይ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮችና አባቶች የተሣተፉበት ደማቅ የአፍጥር ምሽትም ተካሂዷል።
በህብረ-ብሔራዊ የታጀበው ፍቅርና አንድነቱ በሁሉም የድሬዳዋ አካባቢዎች የቀጠለ ሲሆን በዚህም የተቸገሩትን የመርዳትና የመደገፍ ሥራም ተጠናክሮ እየተሰራ ነው። ይህ የድሬዳዋ መለያና መገለጫ የሆነውን ድንቅ እሴት ድሬዳዋ እንደ ከተማ ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 120 ዓመታት ዘልቆ ቆይቷል። የከተማዋ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት መገለጫም ነው ማለት ይቻላል።
በእርግጥ ህወሓት በበላይነት ሲመራ በነበረው የኢህአዴግ መንግስት ዘመን ይህ የህዝቦች አብሮነትና ፍቅር እንዲሸረሸር ብርቱ ሥራ በመከናወኑ በነዋሪዎች ውስጥ የልዩነት ስንጥቃት መፍጠሩ የሚካድ አይደለም።
ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት ዋንኛው መሰሶው ነዋሪዎቿ ለዘመናት ያዳበሩት ፍቅርና አንድነት መሆኑን ይበለጥ ገንዛቤ በመያዙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለድሬዳዋ መገለጫ የነበረው ፍቅር፣ ሕብረትና አንድነት ወደ ቦታው እየተመለሰ ይገኛል፡፡
ይህን ልዩ ውበትና የተጋመደ ማንነት አፅንቶ መጠበቅና ለተተኪው ትውልድ ማውረስ ለድሬዳዋም ሆነ ለነገ ጠንካራ ኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ለጎዳና ተዳዳሪዎች የበጎ ፍቃድ ተግባር ያከናወኑት የስካውት ፌደሬሽን ወጣቶችና አባላት ናቸው።
የፌደሬሽኑ ኮሚሽነር ወጣት አማረ ጥላሁን "መረዳዳትና መደጋገፍ፣ የተቸገሩትን መጠየቅ ከተረፈ ሣይሆን ካለን ጭምር አካፍለን መብላት፣ ከአያቶቻችን ጀምሮ መገለጫችን ነው" ይላል። በዚህም እሱና ጓደኞቹ በእውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ጎዳና ላይ ለሚኖሩ እህት-ወንድሞች፣ አባቶችና እናቶች የአቅማቸውን እየደገፉ ነው። ይህን በጎ ተግባር በየሣምንቱ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገረው።
"ከህብረተሰቡ ያሰባሰብነው 16 የማዳበሪያ ከረጢት አልባሳትና ጫማዎችን አከፋፍለናል፣ ከ500 በላይ ሰዎችን ፀጉር አስተካክለናል፤ የአንድ ሰው ፀጉር በክፍያ ይስተካከል ቢባል ትንሹ ዋጋ 50 ብር ነው›› ብሏል፡፡
ወጣቱ እንዳለው አሁን እንደአገር የገጠመንን ችግር ለመሻገር ያሉትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሃብቶች እንዲሁም እውቀትን በተግባር ማዋል፣ እርስ በርስ መደጋገፍና መረዳዳት ያስፈልጋል።
ይህ ለድሬዳዋ አዲስ አይደለም፤ ለአገርና ለአካባቢ ዘላቂ ሰላምና ልማት ዕውን መሆን መደጋገፍ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክቷል።
"በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሚታዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ተባብሮ መቆም እንደሚያስፈልግና ይህም ራስን፣ ቤተሰብንና አገርን አጽንቶ ማሻገር መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ሌላዋ በበጎ ሥራ የተሰማራችው ተማሪ የትናየት አለሙ ናት።
"ባይኖርህም ፍላጎቱ ከውስጥ ከመነጨ ሰውን መርዳት ይቻላል። ይህ ደግሞ ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ዋጋ ስላለው የህሊና ደስታ ይሰጣል፡፡ ሰዎች በጎ በማድረግ የሚገኘውን ጥልቅ ደስታ ቢያጣጥሙ ደስ ይለኛል" ያለችው ወጣቷ፣ ግለሰቦችን አስተባብረው አምስት የፀጉር ማሽን በመግዛት የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትን ጭምር ጸጉር በመቁረጥ መደገፋቸውን ገልጻለች።
ወጣቶቹ ካሳመሯቸው መካከል አቶ መሐመድ ሀሰን በወጣቶቹ የተደረገላቸውን በጎ ተግባር መቼም እንደማይረሱት ተናግረዋል።" እንደዚህ ብንደጋገፍ ድሬዳዋን ከፍ ማድረግ እንችላለን፤ እኔ ብቻ ሣልሆን ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ህጸናት ሁሉም ተደስተዋል" ሲሉም አክለዋል።
ታህሳስ 18 ቀን 1895 ዓ.ም ከጅቡቲ "ሸክተፍ! - ሸክተፍ! " እያለ የአሁኑ ምድር ባቡር አደባባይ የደረሰው ባቡር ድሬዳዋ እንደ ከተማ ታንጻ ታብብ ዘንድ ጉልህ አበርክቶ ነበረው።
ድሬዳዋ ከጽንሰቷ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባቡርን ተከትለው የመጡ የተለያዩ የውጭ አገራት ዜጎች ጭምር መኖሪያ ሆና እያገለገለች ነው፡፡
በውስጧ የሚኖሩና እርስ በርስ የተጋመዱ ነዋሪዎቿ ደግሞ የፈጠሩት ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለሌሎች ምሳሌ ነው፤ ባይተዋርን ጎትቶ ያስቀራል። ለስራ፣ ለንግድ ወደ ሆዷ የገባ እንግዳ ሁሉ ድሬዳዋን ዘላቂ መኖሪያው የሚያደርጋትም በዚህ ፍቅሯ ሣቢያ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ።
ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የገጠርና የከተማ ነዋሪዎቿ በኃዘን፣ በችግርና በደስታ ጊዜያት ሁሉ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትና በጋራ የመቆም እሴትና ዝንባሌን አፅንተው እንዲዘልቅ ታትረዋል፡፡
በዚህ በተያዘው የረመዳን ጾም ለገሃር አደባባይ የታየውም ይሄው እውነታ ነው፡፡
"በይበልጥ እንድንፋቀር ኑ በጋራ እናፍጥር" በሚል መሪ ሃሳብ ድሬዳዋ በተፀነሰችበት የምድር ባቡር አደባባይ የተካሄደውንና የሁሉም ኃይማኖት ተቋማት አባቶችና ዑላማዎች፣ የአስተዳደሩ ከንቲባና ካቢኔ አባላት የተሣተፉበትን ደማቅ ምሽት ያዘጋጁት ወጣቶች ናቸው፡፡
ከወጣቶቹ አንዱ ኢዮብ ሐሰን ለኢዜአ ሪፖርተር እንዳለው በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመሻገር ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበርና መደማመጥ አለባቸው ፡፡
እርስ በርስ ለመደማመጥ ደግሞ የእዚህ አይነቱን መድረክ መፍጠርና ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
በልዩነት ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የህብረ-ብሔራዊ አንድነት ከተማ መሆኗን ለዓለም ለማሳየት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ተመሳሳይ መንፈስ ያንጸባረቁትና በከተማ ነዋሪ ዘንድ ተቀባይት ያተረፉት ሼህ አሚን ኢብሮ "የሁሉም የእምነት አባቶች በጋራ ሆነን እንደበላነው ሁሉ ይህ ትብብርና አንድነታችንን በድርቅና በጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርደትና መልሶ ለማቋቋም ማዋል ይኖርብናል" በማለት አሳስበዋል።
የፆም ወር የተቸገሩትን መርጃ፣ የታመሙትን መጠየቂያ፣ የታረዙትን ማልበሻ በመሆኑ ካለችን ለተቸገሩ በማካፈል እንደ አገር የገጠመውን ችግር ተዛዝኖ መሻገር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
"የድሬዳዋ ፍቅርና አንድነት ፀንቶ ለትውልድ እንዲተላለፍና አገር የገጠማትን ወቅታዊ ችግር ለመሻገር የሃማኖት አባቶች በሁሉም ዘርፍ ተቀናጅተን እንሰራለን" ያሉት ደግሞ ወንድም ሚልኪያስ ታዬ ናቸው።
ለዘላቂ ሰላም፣ ለአገር ልማት ዳር መድረስ ሁሉም በየመስኩ ኃላፊነቱን የሚወጣበት ወቅት መሆኑን ነው የገለጹት።
"ከተማችን በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በብሔር ሣንለያይ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ፀንቶ ያበበባት መሆኗን ለዓለም ህዝብ በተግባር በማሳየታችን እንኮራለን" ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ-ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት ይህን የህዝብ አንድነት በማጠናከር ለአገር ሰላምና ልማት እንዲሁም የተቸገሩትንና የተጎዱ ወገኖች መልሶ ለማቋቋም መስራት ይገባል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የታደሙት ነዋሪዎች ከሦስት ዓመት በፊት የነበረው የርስ በርስ ጥልና መካሰስ ሰክኖ ለአገር ምሳሌ የሆነችው ድሬዳዋ ወደ ዝናዋ እየተመለሰች በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል
አቶ ታደሰ አለሙ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "ለትልቁ ዝግጅት ኬክ ደፍቼ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የታደምኩት ይህ ማንነታችን ፀንቶ እንዲጠናከር ስለምፈልግ ነው" ብለዋል።
በቀጣይ ይህ የህዝብ አንድነት እንዲፀና አስተዳደሩን የሚመሩት አካላት የህዝብ ጥያቄዎችን በየጊዜው እንዲያዳምጡና ጥያቄዎቹን ለመመለስም በሃቅ እንዲሰሩ አመልክተዋል።
ባለፈው ቅዳሜ በተዘጋጀው በጋራ የማፍጠር ሥነ-ሥርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና የካቢኔ አባላት እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተሳትፈዋል።
ከንቲባ ከድር ጁሃር ለአገርና ለዓለም ምሳሌ የሚሆነውን ጠንካራ የህዝቦች ትስስር፣ አንድነትና ፍቅር ጠብቆ አገርን ለማሻገር ማዋል እንደሚገባ መክረዋል።
"ያለንን ሃብት በአግባቡ በመረዳት አንድነታችንን አጠናክረን የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ እንሰራለን" ሲሉም ገልጸዋል።
አስተዳደሩ በህዝባዊ ውይይት ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አደረጃጀትና አሠራር ከመዘርጋት ባለፈ ወሳኝ የሰው ኃይል መልምሎ ወደተግባር መግባቱን ጠቁመዋል።
ከህዝብ ጋር በመቀናጀት አገርን ለማሻገር የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ወጣቶች በሁሉም አደረጃጀቶች ለሰላምና ለልማት መረጋገጥ የጀመሯቸውን ሥራዎች እንዲያጠናክሩ ከንቲባ ከድር ጥሪ አቅርበዋል።