ህገ-ወጥ የግብይት ሰንሰለት ለሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጥ የግብይት ሰንሰለት ለሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት ሆኗል
መጋቢት 29/2014 (ኢዜአ) ህገ-ወጥ የግብይት ሰንሰለት ሰው ሰራሽ የሆነ የዋጋ ንረት እንዲባባስ ምክንያት መሆኑን በአዲስ ወግ የአንድ ጉዳይ ወርሃዊ የውይይት መድረክ ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ አዲስ ጉዳይ ወርሃዊ መድረክ "የኑሮ ውድነት መንስኤዎቹ እና የመፍትሔ እርምጃዎች" በሚል ርዕስ ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ መለሰ ምናለ፣የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የኅብረት ስራ ግብይት ዳይሬክተር ይርጋለም እንየውና የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል።
አቶ መለሰ ምናለ በዚህ ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመረ በመጣው የዋጋ ንረት በዜጎች ኑሮ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምርት ስርጭትና ግብይት ስርዓት ችግር፤ የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም፣ ከዓለም አቀፍ ወቅታዊ ሁኔታ የሚመጣ የዋጋ ጭማሪ እንዲሁም የበጀት አስተዳደር ጉድለት ለኑሮ ውድነቱ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።
አያይዘውም አሁን የገጠመው ሁኔታ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር በጀመረበት የመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት አጋጥሞ ከነበረው ችግር ጋር ተመሳሳይ እንደነበር አስታውሰው፤ ችግሩ በአንድ ወገን ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ በጋራ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የኅብረት ስራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው በበኩላቸው የግብይት ስርዓቱ ችግር ለዋጋ ንረቱ መንስኤ መሆኑን ገልፀዋል።
የግብይት ሰንሰለቱ አምራቹንም ሆነ ሸማቹን ተጠቃሚ እንደማያደርግ ገልፀው፤ በግብይት ሂደቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት ህገ-ወጥ ደላሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ እሴት የማይጨምሩ መሀል ላይ ያሉ ህገ ወጥ የግብይት ሰንሰለቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነትን እያባባሱ ያሉ ህገ-ወጥ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ፤የህዝብ ቁጥር መጨመር እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገት ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆንም ለዋጋ ንረቱ አባባሽ ምክንያት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በሀገር ውስጥ የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በተለይ ለውጥ እያመጣ ያለውን የበጋ መስኖ ልማት አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚችሉ ኢንደስትሪዎችን በማስፋት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል መስራት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡
በውይቱቱ ላይ ሀሳባቸውን ያካፈሉት አምባሳደር አባቢ ደምሴ፣ ኃያላን ሀገራት ጂኦ-ፖለቲካውን ለመቆጣጣር እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ የዓለም የንግድ ሰንሰለትን እንዳዛባው ተናግረዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት ደግሞ የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም በኢትዮጵያ አጋጥሞ ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር ተደምሮ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው አብራርተዋል፡፡
ከገንዘብ ሚኒስቴር የመጡት አቶ ኤፍሬም ወልደ ስላሴ በበኩላቸው መንግስት መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ የታየውን የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ምርቶች ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በተለይ ለሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት በሆኑት ህገወጥ ደላሎች ላይ አስተማሪ ቅጣት መተላለፍ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
ችግሩ በመንግስት ጥረት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡