ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ያደረገችው አስተዋጽኦ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር ነው

መጋቢት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ያደረገችው አስተዋጽኦ የአፍሪካ ቀንድ አባል አገራት ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን ገለጹ።

እ.አ.አ በ2011 ዓ.ም ራሷን ችላ ሀገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ማምራቷ ይታወሳል።

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ግጭት ውስጥ የቆየችው ደቡብ ሱዳን ወደ ሰላም እንድትመለስ ብዙ ድርድርና ሽምግልና ሲካሔድ ቆይቷል፤ በሂደቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ሚናዋ የጎላ ሆኖ ይነሳል።

በቅርቡም በአገሪቷ የተደረሰው ስምምነት ለሰላም ተስፋን የሚያጭር አዲስ ጅማሮና ለቀጣናውም ጥሩ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ታምኗል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ አገራቱ በሰላምና ጸጥታ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ማህበራዊ ዘርፍ ለመተሳሰር እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሰላም አየር እንዲነፍስበት የሁለቱ አገራት በጋራ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አንስተዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ከገባችበት የሰላም እጦት እንድትወጣ ያልተቆጠበ ድጋፍ ስታደርግ ነበረች ብለዋል አምባሳደር ጀምስ።

በቀጣይም የአፍሪካ ቀንድ አባል አገራት ሰላም እንዲሰፍንና የተሻለ ትብብርና ትስስር እንዲኖር ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ሚናቸውን ይወጣሉ ብለዋል።

አምባሳደር ጀምስ አፍሪካ በአጀንዳ 2063 አማካኝነት የበለጠ ለማስተሳሰርና በጋራ ለማደግ እየሰራች መሆኑንም አስታውሰዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የአፍሪካ ቀንድ አባል አገራት በቅድሚያ እርስ በርስ መተሳሰርና መተባበር አለባቸው ይላሉ።

በቀጣናው ያለው ትስስር እውን እንዲሆን ደግሞ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ትወጣለች የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

እንደ አምባሳደር ጀምስ ገለጻ ሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

ከተፈረሙ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለቱን ሀገራት የሚያስተሳሰር የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚሁ ፕሮጀክት ትግበራ የደቡብ ሱዳን ልኡክ ከሰሞኑ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣም ተናግረዋል።

የመንገድ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር የሚጠናከር መሆኑንም ነው ያነሱት።

ይህ ብቻ ሳይሆን ሁለቱ ሀገራት በሃይል አቅርቦት፣ በነዳጅና ሌሎች ዘርፎች ትስስሮችን ለማስፋት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም