ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በእዳ ጫና ቅነሳ እና በግብርና ልማት ዘርፍ የተሳካ ውጤት አስመዘግባለች

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በእዳ ጫና ቅነሳ እና በግብርና ልማት ዘርፍ የተሳካ ውጤት ማስመዝገቧን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህሩ ዶክተር ብርሃኑ ደኑ ተናገሩ።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በኢኮኖሚ ዘርፍ የታዩ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮችን በማስመልከት በዩኒቨርሲቲው ንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ብርሃኑ ደኑ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት አራት ዓመታት በጸጥታ ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ ድርቅና የተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም በኮሮና ወረርሽኝ መፈተኑን አንስተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች፣ አገር አፍራሾች ጠመንጃ አንግበው ጦርነት የከፈቱበት፣ የተፈጥሮ አደጋና ድርቅ የኢትዮጵያ ተደራራቢ ፈተናዎች ነበሩም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በእነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ሆና የተሻለ ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት ላይ ትገኛለች ነው ያሉት።

በተለይ የውጭ ዕዳ ጫናን በመቀነስ የተከተለችው ስትራቴጂ በአጭር ጊዜ የተሻለ ውጤት ተመዝግቦበታል ብለዋል።      

በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚም ባለፉት አራት አመታት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡  

በተለይም ስንዴን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጭምር በመታገዝ በመስኖ በማምረት ሂደት የታየው ቁርጠኝነት ስኬት የታየበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የተለያዩ ሴክተሮች ለግሉ ዘርፍ ክፍት እየተደረጉ በመሆናቸው በቴሌኮም ዘርፍ የውጭ ኩባንያ መግባቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በሌላ መልኩም ለረጅም ዓመታት የቆዩ እና የወቅቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የማይዋጁ የተለያዩ ህጎች እንዲሻሻሉ መደረጋቸውም የለውጡ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።  

ከ1960ዎቹ ጀምሮ ስራ ላይ የነበረው የንግድ ህግ ተሻሽሎ ወቅቱን በሚመጥን መልኩ መዘጋጀቱና በአንዳንድ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የነበረውን ኋላ ቀር አሰራር ዲጂታላይዝ ማድረግ የተሰራው ስራም የላቀ ውጤት የታየበት መሆኑን ጠቅሰዋል።   

በተለያዩ ተቋማት ላይ የተከናወነው የሪፎርም ስራም ተስፋ የሚታይበት በመሆኑ እስከ ታች ወርዶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት እነዚህና ሌሎችንም ስኬቶች ብታስመዘግብም ተጋርጠውባት የነበሩ በርካታ ችግሮች በለውጡ ሂደት በታሰበው ልክ ውጤት እንዳይመጣ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የጸጥታ ችግር፣ የስራ አጥነት እና አሁንም ያልተሻሻለው የኑሮ ውድነት ባለፉት አራት አመታት ቀላል ፈተናዎች አልነበሩም።

እነዚህና መሰል ችግሮች አሁንም የቀጠሉ በመሆናቸው ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ አሰራሮችን መከተል እንደሚገባ ዶክተር ብርሃኑ አመላክተዋል።  

በተለይም ከውጪ በብዛት የሚገቡ የፍጆታ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ እንዲመረቱ የማድረግ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ነው ያሉት።     

የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠርና የኑሮ ውድነት ከዚህም እየተባባሰ እንዳይሄድ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም