የጉራጌ፣ ሀድያና ስልጤ ዞኖችን የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታ መጓተት በኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሯል-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጉራጌ፣ ሀድያና ስልጤ ዞኖችን የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታ መጓተት በኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሯል-ነዋሪዎች
ሀዋሳ መጋቢት 29/2014 (ኢዜአ) የጉራጌ፣ ሀድያና ስልጤ ዞኖችን የሚያገናኘው ከአጣጥ ሌራ 81 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ በመጓተቱ በእለት ተለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ጫና መፍጠሩን ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በበኩሉ የመንገዱን ግንባታ ያጓተተው ተቋራጭ ውል ተቋርጦ ለሌላ ተቋራጭ ለማስተላለፍ በጨረታ ሂደት ላይ በመሆኑ ነው ብሏል።
ከአጣጥ ሌራ ሶስት ዞኖችን የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታን በሶስት ዓመታት ጊዜ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ በ2010 ዓ.ም ወደስራ መገባቱ ተነግሯል።
የእነሞርና ኤነር ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ፍቃዱ አምዛ ለኢዜአ እንዳሉት የመንገዱ ግንባታ መጀመር አካባቢው የተለያዩ የግብርና ምርቶች የሚመረቱበትና ለቤት ግንባታ የሚውል አጣና በብዛት ወደ መሀል አገር የሚቀርብበት በመሆኑ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
"ይሁንና የመንገዱ ግንባታ ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ ከመቋረጡ ባለፈ ለግንባታው ተብሎ በየቦታው የተቆፋፈሩ የመንገዱ ክፍሎች ለእንቅስቃሴ አስችጋሪ በመሆን ለአደጋ እያጋለጡን ስለሆነ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ይፈልግልን " ሲሉ ጠይቀዋል።
የእነሞርና ኤነር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ግርማ እንደገለጹት መንገዱ በሶስት ዓመት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጀምርም ሳይጠናቀቅ አምስት ዓመት ሆኖታል።
በየቦታው ተቆፋፍረው ሳይሰሩ የዘገዩ የመንገዱ ክፍሎች በሰዎችና በተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ጠቅሰው ግንባታው ስለመዘግየቱ ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያቀርብም ምላሽ ባለማግኘቱ በህዝቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማስነሳቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የአጣጥ ሌራ መንገድ ፕሮጀክት ስራ እስኪያጅ አቶ ተማም ኡመር ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ መገንባት ባለመቻሉ ለተቋራጩ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጥም በአቅም ማነስ ምክንያት ለውጥ ባለመምጣቱ ውሉ መቋረጡን ተናግረዋል።
ግንባታውን ለሌላ ተቋራጭ ለመስጠት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በራሱ አቅም ዝናብ ሲጥል ለህብረተሰቡ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ የሚሆኑ የመንገዱን ክፍሎች በመለየት የግንባታ ስራ መጀመሩን አመልክተዋል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው መንገዱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ግንባታውን ከያዘው ተቋራጭ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ እንደነበር ተናግረዋል።
ጥረቱ መፍትሄ ማምጣት ባለመቻሉ ውሉን በማቋረጥ እስካሁን የተሰሩና ቀሪ ስራዎችን በመለየት ለአዲስ ኮንትራከትር ለመስጠት ጨረታ እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ የመንገዱ ግንባታ መንግስት ባስቀመጠው ፍጥነትና በተያዘው እቅድ መሰረት ያልተሰራበትን ሁኔታ በመገንዘብ ሌላ ተቋራጭ ወደ ስራ እስከሚገባ ድረስ በትዕግስት መጠበቅና ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።