በደሴ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ነዋሪዎች አትክልትና ፍራፍሬ ለገበያ እያቀረቡ ነው

124

ደሴ (ኢዜአ) መጋቢት 29/2014---በከተማ ግብርና በአካባቢያቸው በቀላሉ ያመረቱትን አትክልትና ፍራፍሬ ከራሳቸው አልፎ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን በልማቱ እየተሳተፉ ያሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ለቤት ውስጥ ፍጆታ አትክልትና ፍራፍሬ ለመግዛት ከ300 ብር በላይ በየወሩ ያወጡ እንደነበር በደሴ ከተማ በልማቱ የተሳፉት አቶ ሰይድ እንድሪስ ለኢዜአ ገልጸዋል።

አትክልትና ፍራፍሬ በአካባቢያቸው በቀላሉ ማምረት እንደሚችሉ ከከተማ አስተዳደሩ ባገኙት ስልጠና መሰረት ወደ ተግባር መግባታቸውን አስረድተዋል።

በልማቱ 72 ሆነው በመደራጀት ወደስራ እንደገቡ የገለጹት አቶ ሰይድ፣ ቆሻሻ መጣያ የነበረ ቦታን በማጽዳት አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

እያንዳንዳቸው በወር ከ800 ብር በላይ የሚገመት አትክልት እንደሚጠቀሙ ገልጸው፣ ለጎረቤት ጭምር አካፍለው ለገበያም እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

"በትንሽ ቦታ አምርቶ ተጨማሪ ገቢ ማግኘትና ትኩስ ምርት መጠቀም እንደሚቻል ተረድተናል" ያሉት አቶ ሰይድ፣ በአካባቢ ምርት ገበያውን ለማረጋጋት በአሁኑ ውቅት ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላዋ የቀበሌ 08 ነዋሪ ወይዘሮ ኢክራም ይመር እንዳሉት፣ በአካባቢያቸው የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ እያመረቱ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለገበያ እያቀረቡ ነው።

"ዘርፉ አዋጭ፣ በቀላሉ መመረት የሚችልና ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን በራሴ አረጋግጫለሁ፤ ሥራውን አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያ፣ ቀይ ስር፣ ካሮትና ሌሎችን አትክልቶችን እያመረቱ መሆኑን ጠቁመው፣ በዓመት ሶስት ጊዜ በማምረት ለሌሎች ምሳሌ መሆናቸው ገልጸዋል።

"በወዳደቁ ፕላስቲኮች አፈር ጨምረን በየግድግዳውና በር ላይ በምናመርተው አትክልት ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ በጥቂት ቦታ ማልማት እንደሚቻል በተግባር አሳይተናል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ህይወት ዳምጠው ናቸው።

"የመንግሥት ሠራተኛ ብሆንም በስልጠና ያገኘሁትን ተሞክሮ ተጠቅሜ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመንና ቀይ ስር በቤቴ እያመረትኩ ወጪን ማስቀረት ችያለሁ" ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው ተረፈ እንዳሉት ህብረተሰቡ በየአካባቢው በከተማ ግብርና በሚያመርተው አትክልትና ፍራፍሬ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ አልፎ ገበያውን እንዲያረጋጋ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

በዘርፉ ከ280 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸው፣ "የእነሱን ልምድ በማስፋት ሌሎችም እየተሳተፉ ይገኛል" ብለዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ተሳታፊዎቹ የቆሻሻ መጣያ የነበሩ ስፍራዎችን፣ በግቢ ውስጥ ያለ ክፍት ቦታ፣ በጋራ መኖሪያ ህንጻዎችና በየግድግዳው ላይ ጭምር አነስተኛ ቁሶችን ተጠቅመው እያመረቱ መሆኑን ገልፀዋል።

"በከተማ ግብርና እንቅስቃሴው ከራሳቸው ተርፎ ለገበያ እያቀረቡ በመሆኑ ዘርፉ ገበያውን ለማረጋጋት እያገዘ ነው" ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር በማቅረብ ዘርፉ እንዲጠናከር እየተደረገ ነው።

በብዛት ለሚያመርቱት በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ህብረተሰቡ ምርቱ ያለበት በመሄድ መግዛት መጀመሩንም ጠቁመዋል።

በከተማ ግብርና ከ800 ለሚበልጡ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም