ተመራቂ ተማሪዎች ያጎለበቱትን የህብረ ብሔራዊ እሴት ለሀገራዊ አንድነት ሊጠቀሙበት ይገባል

84

ሆሳዕና (ኢዜአ) መጋቢት28/2014---ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያጎለበቱትን የህብረ ብሔራዊ አንድነት እሴት በማጠናከር በቀጣይ ለሀገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መጎልበት እንዲጠቀሙበት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት አሳሰቡ።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት በመቋረጡ ምክንያት ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን ከ270 በላይ ተማሪዎች አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በሥነሥርዓቱ ላይ እንዳስገነዘቡት ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያጎለበቱትን የህብረ ብሔራዊ አንድነት እሴት ለሀገራዊ እንድነትና ዘላቂ ሰላም መጎልበት ለጠቀሙበት ይገባል፡

አሸባሪው ህወሓት ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ጦርነት ለኩሶ ዜጎችን ለጉዳት መዳረጉን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ሀገር ለማፍረስ ቆርጦ በመነሳቱም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጭምር ኢላማ ማድረጉን አስታውሰዋል።

"በዓለም አቀፍ የጦር ህግ ተቀባይነት የሌለው ተግባር በመፈጸምም ጭካኔውን አሳይቷል" ብለዋል።

በእዚህም ትውልድ ለመቅረጽ በከፍተኛ ሀብት የተገነቡ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ስራቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስታውሰዋል፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲም እንደ ሀገር የደረሰውን ችግር ለመጋራት ከ1 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ በዩኒቨርስቲው ላይ የራሱን ተጽእኖ ቢያሳድርም በሌላ በኩል ተማሪዎች የአክሱምን እና የሀድያ ህዝብን እሴት እንዲያውቁ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተመስገን ቶማስ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች ፈተናዎችን ተቋቁመውና ከተስፋ መቁረጥ ወጥተው ለዚህ ቀን መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

"የሰላምን ዋጋ ምን ያክል ከፍተኛ መሆኑን በፈተናዎች መካከል ያለፉ ተመራቂዎች ይረዳሉ" ያሉት ዶክተር ተመስገን፣ ምሩቃን ወደ ማህበረሰቡ ሲሄዱ በሰላም ግንባታ ላይ ህብረተሰብ እንዲያነቁ አስገንዝበዋል ፡፡

ለመመረቅ አንድ ሴሚስተር ሲቀራቸው የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ትምህርታቸው መቋረጡንና በእዚህም ተስፋ ቆርጣ እንደነበር በማርኬቲንግ ማናጅመንት የተመረቀችው ተማሪ ናርዶስ ደርብ ገልጻለች።

በመንግሥት እገዛ ትምህርቷን በዋቸሞ ዩንቨርሲቲ ቀጥላ ዛሬ ለምረቃ በመብቃቷ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማትም ተናግራለች፡፡

ተማሪዋ እንዳለች ወደ ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ከመጣች በኋላም ያገኘችውን የአብሮነት እሴት በቀጣይም ታጠናክራለች፡፡

"ሀገር ሰላም በሌለበት በአግባቡ ለመተንፈስ ከባድ መሆኑን የተረዳሁበት ወቅት ቢኖር በጦርነቱ ወቅት ነው" ያለው ሌላው ከባዮ ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ተመራቂው ተመስገን በቀለ ነው።

በሀገር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም