ኢቢሲ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ መወጣት የሚገባውን ድርሻ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢቢሲ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ መወጣት የሚገባውን ድርሻ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
መጋቢት 28/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /ኢቢሲ/ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ መወጣት የሚገባውን ድርሻ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሰራተኞች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱም ተቋሙ ያለው አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና ቀጣይ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ውይይት ተካሂዷል።
የምክር ቤቱ አባላት በተለይም ተቋሙ አንገብጋቢ የህዝብ ችግሮችን ወደ መንግስት፤ የመንግስትን ሐሳብ ደግሞ ወደ ሕዝብ ማቅረቡን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
ተደራሽነትን በተመለከተ ተቋሙ ከዚህም በላይ ሊሰራ እንደሚገባው ነው አባላቱ በውይይቱ ላይ ያነሱት።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግሥቱ እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ከማዋል ባሻገር የሰው ኃይል ማብቃት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።
ትክክለኛና ፈጣን መረጃ ለህዝቡ ተደራሽ ማድረግ ከተቋሙ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ያስገነዘቡት ሰብሳቢዋ አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ተቋሙ የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በህዝቡ ውስጥ ትኩረት የሚሹ አንገብጋቢ ጉዳዮችን ለይቶ የህዝብ ድምጽ በመሆን በኩል የበለጠ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ወቅቱን የሚመጥን ቴክኖሎጂ መጠቀም ኮርፖሬሽኑ ተደራሽነቱን ለማስፋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ብርድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ተወዳዳሪነቱን ለመጨመር አዳዲስ ማሰራጫ ስቱዲዮችን እየገነባ ነው።
በተለይ በሰው ኃይል በኩል ሰራተኛው አቅሙን የሚገነባበት ሁኔታዎች ተመቻችተው ሥልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ነገር ግን "ተቋሙ የህዝብ ድምፅ መሆን ላይ ክፍተት እንዳለበት እንገነዘባለን" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዲያም ሆኖ መልካም አስተዳደር ላይ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ተቋሙ በዘገባዎቹ ጥቆማ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በመሉ በራሱ ገቢ እንዲተዳደር መደረጉ ጫና መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ፍሰሃ በተለይ በበጀት በኩል የመንግሥትን ድጋፍ እንሻለን ብለዋል።
የኮርፖሬሽኑ ሚዲያ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ በለጠ እሱባለው ተቋሙ ተደራሽነቱን ለማስፋት ተጨማሪ ማሰራጫ ስቱዲዮችን እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀረርና ባህርዳር እየተገነቡ ያሉ ስቱዲዮች በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩም ጠቅሰዋል።