ቀጥታ፡

በአሶሳ እና አካባቢው የተቋረጠውን የኤሌትሪክ መብራት አገልግሎት ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው

አሶሳ ፤ መጋቢት 28/2014(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ዞን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ በደረሰ ጉዳት በአሶሳና አካባቢው የተቋረጠውን አገልግሎት ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ነጋሳ ደሳለኝ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ትናንት ምሽት ነፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ  ተከትሎ ነው ጉዳቱ የደረሰው።

በዚህም ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ 132 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያስተላልፉ መስመሮችን የተሸከሙ ማማዎች በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ መንደር 48 እና 49  ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው  ገልጸዋል።

ከፍተኛ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች መውደቅን  ተክትሎ አሶሳ ከተማና አካባቢው  የኤሌክትሪክ  መብራት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ተናግረዋል።

ፈጣን ጥገና በማድረግ አገልግሎቱን እንደገና ለማስቀጠል  ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ምዕራብ ሪጅን ጋር በመቀናጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን  አቶ ነጋሳ  አስታውቀዋል።

ከደረሰው ጉዳት አንጻር ጥገናው በእዚህ ቀን ይጠናቀቃል ብሎ መናገር ባይቻልም  አገልግሎቱን ፈጥኖ ለማስቀጠል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ  መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም