ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ለንግዱ ማሕበረሰብ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት የ'ኦን ላይን' ስርዓት ይፋ አደረገ

መጋቢት 28/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት ለንግዱ ማሕበረሰብ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት የ'ኦን ላይን' ስርዓት ይፋ አደረገ፡፡

የ'ኦን ላይን' ስርዓቱ ምክር ቤቱ ለንግዱ ማሕበረሰብ የሚሰጠውን አገልግሎቶች በአካል መምጣት ሳያስፈልገው ተገልጋዩ ባለበት እንዲያገኝ ያስችላል ተብሏል።

ስርዓቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስትር ዴኤታው አቶ እንዳለው መኮንን እንዳሉት፤ በአስር አመት የልማት እቅድ ከተያዙ ግቦች መካከል አንዱ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሆኑን አስታውሰዋል።  

 

ይህንኑ ለማፋጠን አገሪቷ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ቀርፃ፤ ለትግበራ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ሂደትም የግሉ ዘርፍ ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረው፤ ሚኒስቴሩ ዘርፉን ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ምክር ቤቱ አሰራሩን ከወረቀት ወደ ዲጂታል ማዘመኑ የንግዱ ማህበረሰብ ባለበት ቦታና በተመቸው ጊዜ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል በመሆኑ የሚበረታታ ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተጠባባቂ ዋና ፀሓፊ አቶ ውቤ መንግስቴ በበኩላቸው፤ መንግስት የያዘውን የ'ዲጂታላይዜሽን' አካሄድ በማጠናከር የንግድና የምርት ስራን በቴክኖሎጂ መደገፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ይፋ ያደረገው የ'ኦን ላይን' ስርዓትም የ'ዲጂታላይዜሽን' ስራን የሚያግዝ ከመሆኑ ባለፈ የንግዱ ማሕበረሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት የተፋጠነና ወጪ ቆጣቢ ያደርገዋል ብለዋል።

የ'ኦን ላይን' አሰራር ስርዓቱ የምክር ቤቱ አባላት የሚፈልጉትን አገልግሎቶች ባሉበት ሆነው እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የ'ኦን ላይን' አሰራሩ የንግድ ስርዓቱን በማሳለጥ ለአህጉራዊና ቀጣናዊ ትስስር አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።

ስርዓቱ ንግድና ኢንሸስትመንት ለማስፋፋትና የአቅም ግንባታ ስራዎችንና ለማቀላጠፍ እንደሚረዳም ነው  አቶ ውቤ የገለፀት።

የ'ኦን ላይን' ስርዓቱ በአንድ ዓመት ከግማሽ የለማ ሲሆን 2 መቶ 70 ሺህ ዶላር ወጪ ተደርጎበታልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም