ቀጥታ፡

በከተማ ግብርና ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ ሆነናል- አምራቾች

ሐረር ፤ መጋቢት 28 ቀን 2014(ኢዜአ) በከተማ ግብርና ላይ ተሰማርተው እያገኙ ያሉት ምርት ከፍጆታቸው ተርፎ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን በሐረሪ ክልል የከተማ ግብርና ተሳታፊ አምራቾች ተናገሩ።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ አመጋገብን እውን ለማድረግ በቤት ውስጥ የጓሮ አትክልት ሥፍራዎች እንዲኖሩ ማድረግ   ወሳኝ ነው።

በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ በሚውሉ ቁሳቁሶች አማካኝነት ወደላይ የሚዘረጉ የአትክልት ቦታዎችን መሥራት ለብዙኃኑ ቀላል ነው፤ ቤተሰቦች ይህንን የማድረግ አቅማቸውን እንዲፈትሹና እንዲጠቀሙበት አበረታታለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

ኢዜአ በሐረሪ ክልል እየተካሄደ ያለውን የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ ተመልክቷል፤ ይህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ በተግባር የሚያሳይ ነው።

ዘርፉ በሐረሪ ክልል የሚገኘው ነዋሪ ከሸማችነት ወደ አምራችነት በመቀየር የኑሮ ውድነትን ጫና ማቃለል እንደሚችል አንዱ ማሳያ የወጣት መሐመድ ከዛሊ ተሞክሮ ይጠቀሳል።

ወጣቱ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን   በክልሉ አባድር ወረዳ በከተማ ግብርና ተሰማርቶ ውጤታማ መሆን ችሏል።

የከተማ ግብርና የወረስኩት ከቤተሰቦቼ ነው፤በዚህም ትምህርቴን በአግባቡ እየተከታተልኩኝ እኔና 15 የቤተሰቦቼ አባላት መተዳደሪያ አድርገነዋል ሲል ወጣት መሐመድ ለኢዜአ ገልጿል።

በዘርፉ ልማት የሚያገኙት ምርት ከፍጆታቸው አልፎ  በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ በመሆናቸው  በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው  የኑሮ ውድነት ጫና መቋቋም እንደቻሉ ነው የተናገረው።

ከምርቱ ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ መኖሪያ ቤታቸውን አሻሽለው በመገንባት ለተመቻቸ ኑሮ መብቃታቸውን የገለጸው ወጣቱ፤  ሁሉም ባለው አነስተኛ ቦታ ላይም  ቢሆን የጓሮ አትክልት በማልማት እራሱን በምግብ መጥቀም እንደሚችል  ከተሞክሮው  በመነሳት መክሯል።

ወይዘሮ ፍቅርተ ከበደ በበኩላቸው ፤በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ  እንስሳት እያረቡ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያስተዳድሩ ተናግረዋል።

ከአራት ልጆቻቸውና የስራ እድል ከፈጠሩላቸው  ሰባት  ወጣቶች ጋር እያረቧቸው ካሉት የወተት ላሞች በቀን እስከ  100 ሊትር ወትት ለገበያ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

በዚህም የአካባቢውን ማህበረሰብ ፣  እኔና ቤተሰቤን  እየጠቀምኩ ነው፤ ባገኘሁት ትርፍ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች መግዛት ችያለው፣ ልጆቼንም እያስተማርኩ እገኛለው ብለዋል ወይዘሮ ፍቅርተ።

ሁሉም በግቢው ውስጥ ባለው ክፍት ቦታ ላይ የከተማ ግብርና ስራን ቢያከናውን የኑሮ ውድነት ጫናን  ማቃለል እንደሚችል አመልክተዋል።

በክልሉ ከሚገኙ የመንግስት ተቋማት የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ለበርካታ ዓመታት  በከተማ ግብርና ተቋሙንና ማህበረሰቡን እየጠቀመ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽነር ለታ በዳዳ ናቸው።

ታራሚውንም በልማቱ  በማሳተፍ በቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖራቸው በማድረግ  ኮሚሽኑ  እያለማና  እያረመ  ይገኛል ብለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ መሐመድ ኢብራሂም እንዳሉት ፤  በከተማ ግብርና በአትክልት ልማትና  ዓሳ  እርባታ ላይ ተሰማርተው በአንድ ዙር ስራ ብቻ እስከ 250ሺ ብር ድረስ   ገቢ ያገኛሉ፤ ምርቱም  ከእራሳቸውና  ቤተሰባቸው ፍጆታ ተርፎ  ሃብት ማፍራት ችለዋል።

ይህ ተሞክሮ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ሌሎችም በዘርፉ ተሰማርተው ገቢያቸውን ማሳደግ ይቻላሉ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

ዘርፉ  የከተማውን ነዋሪ ከሸማች ወደ አምራችነት በመቀየር  በአሁኑ ወቅት ያለውን የኑሮ ጫና መቋቋም እንዲችል  አቅጣጫ ተቀምጦለት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ  በሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ የከተማ ግብርና ባለሙያ  ወይዘሮ መይሙና ታለገ ናቸው።

የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ፤  የከተማው ማህበረሰብ ባለው አነስተኛ ቦታ  በማምረት  እራሱን በምግብ እንዲችልና ኢኮኖሚውን እንዲደግፍ በተፈጠረው ስራ ውጤት ታይቷል ብለዋል።

ነዋሪውን   እየጠቀመ የሚገኘው የከተማ ግብርና በተቋማት፣ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ስፍራዎች ላይ በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን የማረጋገጡ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  ወይዘሮ ሚስራ  አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም