የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማዘመንና ሙያተኞችን ለማብቃት የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማዘመንና ሙያተኞችን ለማብቃት የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28/2014 /ኢዜአ/ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በአገራቷ የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ሥምምነት ተደረገ።
ሥምምነቱን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መኃመድና የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ፈርመውታል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መኃመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ በርካታ መስኖ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው።
በእነዚሁ ፕሮጀክቶች ውስጥ ቁጥሩ በርካታ የሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ ፕሮጀክቶቹን የማዘመንና ዘርፉን የሚመጥን ቴክኖሎጂዎች መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
በተለይም የሙያተኞች ክህሎት በማሳደግ ረገድ ከሥራና ክህሎት ሚኒስትር ጋር የተጀመረው የተቀናጀ አሰራር ለውጥ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ይህን ተደጋግፎ የመሥራት ሂደት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመው ይህም አገሪቷ ራሷን በምግብ ለመቻል ለምታደርገው ጥረት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቁመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ከስምንት ሚኒስትር ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቀደም ብለው ተገንብተው የነበሩ በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶች በቂ አገልግሎት የማይሰጡበት ሁኔታ መኖሩን አውስተው እነዚህን ፕሮጀክቶች የሚያንቀሳቅሱ ክህሎት ያላቸው ሙያተኞችን ለማሰማራት እቅድ መያዙንም አብራርተዋል።
የመስኖ ልማቱን ለማዘመን የቴክኖሎጂ አቅርቦትና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብና የአስተሳሰብ ግንባታ ሥራውን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ዝግጅት መደረጉንም ነው ያብራሩት።
አሁን ያለንበት ጊዜ የሥራ ባህልን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቃል ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ ቆላማ አካባቢዎች ያሏቸውን እምቅ ኃብት ለማውጣት የሚያስችል የተቀናጀ ሥራ መስራት ይገባልም ብለዋል።