ቀጥታ፡

አለመግባባቶች በመነጋገር እንዲፈቱና በህዝቦች ዘንድ አብሮነት እንዲጎለብት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2014 /ኢዜአ/  አለመግባባቶች በመነጋገር እንዲፈቱና በህዝቦች ዘንድ አብሮነት እንዲጎለብት የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ የተለያዩ የሚዲያ ሃላፊዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ብሮድካስቲንግ አገልግሎት ኤጀንሲ የዲጂታል ሚዲያ መምሪያ ኃላፊ መምህር አቤል አሰፋ፤ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ አብሮነትና ከችግር ለመውጣት በፀሎትም ይሁን በትምህርት እናግዛለን ብለዋል።

የቤተ-ክርስቲያኗ ሚዲያዎችም በአገር ደረጃ ሰላም፣ አብሮነትና አንድነትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ መሆኑን ገልጸዋል።

ቤተ-ክርስቲያኗ አብሮ የመኖር፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የኢትዮጵያዊያን እኩልነት እንዲጎለብት መስራቷን ትቀጥላለች ነው ያሉት።

ለኢትዮጵያ ሰላምና ለህዝቦች አብሮነት መንግስትም ይሁን ሌሎች አካላት ለሚያደርጉት ጥረት የድርሻችንን ሚና ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።

የእስልምና አስተምህሮን መሰረት አድርጎ የተቋቋመው የነሲሐ ቴሌቪዥን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኡስታዝ አዩብ ደርባቸው፤ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት እንዲሁም የመተባበር እሴት እንዲጎለብት የመሥራት ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት ለሚደረገው ጥረት ሁሉ አጋዥና ደጋፊዎች ሆነን እንቆማለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

"ኢትዮጵያ የእኛን የሰላም ቁርጠኝነት የምትሻበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነች" የሚሉት ኡስታዝ አዩብ፤ ለዚህም ስኬት በዱዐም ይሁን በትምህርት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብም በማህበራዊ ሚዲያ በፈጠራና በሐሰት በሚናፈሱ ወሬዎች ሳይደናገር ለአገሩ ታማኝ፤ ለእምነቱ ጠንካራ ሆኖ መቆም አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፤ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ ሚዲያዎች አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ምክክር ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም